ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአማራ ክልል የተገደሉ ከ60 በላይ ንፁሀንን ሞት በተመለከተ የተሰጠ የሀዘን መግለጫ

በየትኛውም ደረጃ እና መልክ የሚደረጉ ጦርነቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን “የጦርነት ህጎችን” ማክበር ይገባቸዋል። ለአብነትም በ1949 እ.ኤ.አ የፀደቀው አራተኛው የጄኔቫ ስምምነት አንቀፅ 3፣ 27 እና 32 ላይ፣ እንዲሁም በ1977 እ.ኤ.አ በተደነገጉት ሁለቱ ፕሮቶኮሎች፣ ፕሮቶኮል I አንቀፅ 48፣51፣57 ፤ ፕሮቶል II አንቀፅ 13 ላይ ‘ንፁሀን ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይደርስ እና ከጥቃትም እንዲጠበቁ’ ያስጠነቅቃሉ። ነገር ግን የብልፅግና አገዛዝ ከፋኖ ኃይሎች ጋር እያደረገ ባለው ጦርነት፣ ንፁሀን አማራዎች በጦርነቱ እየደረሰባቸው ያለው ፈርጀ ብዙ ስቃይ ሳይንስ በሰውአልባ-አውሮፕላን፣ በከባድ መሳሪያዎች እና በእግረኛ ሠራዊት እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ባልደራስን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች እና የሰብአዊ መብት ተቋማት እንዳጋለጡት፣ አገዛዙ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሚያደርገው ጦርነት ጥቃት ሲደርስበት አፀፋ መመለስ በሚል ሰበብ ያልተጠኑ ርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። ለዚህም በመራዊ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። አሁንም በተመሳሳይ በንፁሀን ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ እንደቀጠለ ይገኛል።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር እስቴ እና በጎጃም በሰሜን ሜጫ ወረዳዎች በአንድ ሳምንት ብቻ ቢያንስ ከ60 በላይ ንፁሀን ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ እንደ አይን ምስክሮች ዋቢነት፣ መጋቢት 22/2017 ዓ.ም በጎጃም ሰሜን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ከተማና ዙሪያዋ የአገዛዙ ሰራዊት ቤት ለቤት በመዞር ከ10 ዓመት ህፃን እስከ የ72 ዓመት አዛውንት ድረስ በጭካኔ ገድሏል፡፡ የሜጫ ወረዳ ብራቃት ከተማ እና በዙሪያው የነበሩ የዐይን እማኞች እና የተጎጅ ቤተሰቦች እንዳሉት፣ አድማ ብተና የሚባለው ሀይል እና የመከላከያ ሰራዊት ጦርነት ገጥመው፤ ጥቂት የማይባሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ያገኟቸው ንፁሀን ላይ የበቀል ርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህም ጥቃት ቢያንስ 46 ንፁሀን የተገደሉ ሲሆን በርካቶች መቁሰላቸውን ከተጎጂ ቤተሰቦች ለማረጋገጥ ተችሏል።
በተመሳሳይ በደቡብ ጎንደር ዞን አስቴ ወረዳ ቆማ ንዑስ ከተማ አስመራ ቀበሌ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም አስመራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠገብ አገዛዙ በፈፀመው የድሮን ጥቃት 14 ንፁሀን ተገድለዋል። የብልፅግና አገዛዝ በፈፀመው የድሮን ጥቃት የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ሊሆን እንደሚችል የጠቀሱት የዐይን እማኞች፤ በተፈፀመው ጥቃት ሕይወታቸው ካለፉት ንፁሀን በተጨማሪ 35 የሚሆኑ ንፁሃን በከባድ እና በቀላል መቁሰላቸውን ገልፀዋል፡፡ ከንፁሀን ሰዎች በተጨማሪም የተለያዩ የቤት እና በግጦሽ ተሰማርተው የነበሩ እንስሳት ሳይቀሩ መገደላቸውን የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል።
የብልፅግና አገዛዝ፣ አንድ ሀገር አስተዳድራለሁ ከሚል ሀይል በማይጠበቅ መልኩ፣ በአማራ ክልል እያደረገው ያለው ጦርነት ይበልጥ ደም አቃቢ እና ዘላቂ እንዲሆን እያደረገው ይገኛል። ከዚህ ቀደም በነብሩት እና አሁንም ካሉት ጦርነቶች በመነሳት ስልጣን ላይ ያለው ሀይል ሕውናው ምን ያህል ከጦርነት ጋር የተያያዘ መሆኑን በግልፅ ያሳያል። ከዚህ ቀደም በተደረጉ ጦርነቶች ለተደረጉ ጥፋቶች ተጠያቂ የተደረጉ የፖለቲካ ሹማምንት እና ወታደራዊ አመራሮች አለመኖራቸው፤ አሁን ለሚፈፅሙ ግፎች እንደ አረንጓዴ መብራት እያገለገላቸው ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ቢሆንም፣ አገዛዙም ሆነ ሹማምንቱ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሁኔታ በንፁሃን ደም እጃችው ያለበት ግፈኞች በሙሉ ከሕግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ሊያውቁት ይገባል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በንፁሀን ላይ የሚፈፀምን ግድያ እና በሕዝብ ላይ እየተካሄደ ያለውን አሳፋሪ ጦርነት አስመልክቶ የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች ያቀርባል፦
1. በአገዛዙ የተገደሉ ንፁሀን ፍትህ እንዲያገኙ ሁሉም የሚመለከተው አካል የድርሻውን እንዲወጣ፣
2. የብልፅግና አገዛዝ በሕዝብ ላይ የሚያካሂደው ጦርነት ንፁሀንን ከመግደል እና ጦረኛ ትውልድ ከመፍጠር ውጭ አንዳች ትርጉም እያንደሌለው አውቆ ያሰማራውን ኃይል በአፋጣኝ ከአማራው ክልል አውጥቶ የሀገሪቱን ድንበር በማስጠበቅ ላይ እንዲያተኩር፣
3. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሞትን በየተራ ከመቀበል፣ የሞት ምንጭ የሆነውን አገዛዝ በሰላማዊ መንገድ ለማስወገድ፣ በሰላማዊ ትግሉ እንዲተጋ ባልደራስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በተሰዉት ንፁሀን ሰማዕታቶች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ይመኛል፡፡
የባልደረስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

