እነ እስክንድር ነጋ ለሚያዝያ 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው
የእነ እስክንድር ነጋን ዶሴ የተመለከተው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የፕላዝማ ችሎቱን አካሂዷል። በዚህም ምስክሮቹ በግልፅ ችሎት ይቅረቡ ወይስ ከመጋረጃ ጀርባ ለሚለው ክርክር ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ካሉበት ወህኒ ቤት ሆነው በፕላዝማ ስክሪን ችሎት የቀረቡት የህሊና እስረኞች ምርጫው ሳምንት ሲቀረውም ቢሆን ወጥተው በሰላማዊ መንገድ ለምርጫው አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልፀው አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ ባለፈው ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በቀጠሯቸው መሠረት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይሁን እንጂ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እያከራከረው በሚገኘው የይግባኝ ዶሴ ብይን ባለመስጠቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ያለ አንዳች ውሳኔ መዝገቡን ሳይገልጥ በቀጥታ ለሚያዝያ 28 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።
ከሦስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ባለመገኘታቸው መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ሊዳኝ የነበረው የእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ ለሚያዝያ ስድስት ቀን 2013 ዓ.ም. መራዘሙም አይዘነጋም። በመሆኑም ይግባኝ ለማከራከር የተቀጠረው መዝገብ ሳይከፈት በቀጥታ ለቀጣዩ ችሎት ተዘዋውሮ ነበር።
የህሊና እስረኞች ጠበቆች ዳኞች ከቀትር በኋላ ተሟልተው እንዲቀርቡ፣ ይህ ካልተቻለም በሁለተኛው ቀን እንዲቀርቡ፣ እነኝህን አማራጮች ማድረግ ካልተቻለ ግን ችሎቱ ተከሳሾችን በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል። ሆኖም ዳኞች ውድቅ አድርገውታል።
ባሉበት ወህኒ ቤት ውስጥ ሆነው በፕላዝማ የቀረቡት እነ እስክንድር ነጋ በበኩላቸው ጉዳዩ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር የተያያዘ መሆኑን እና ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያለ ውሳኔ በቀጠሮዎች እየተጉላሉ መሆኑን ጠቅሰው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ስድስት ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአካል መቅረብ ሲገባቸው ችሎቱን በተደጋጋሚ በፕላዝማ እንዲከታተሉ መደረጉም ስህተት እንደሆነ በዕለቱ ተናግረዋል። በዛሬው ችሎትም በድጋሜ ተናግረዋል። በቀጣዩ ችሎት ፖሊስ በአካል እንዲያቀርባቸውም ጠይቀዋል። ሆኖም በቀጣዩ ችሎት በአካልም ሆነበፕላዝማ መቅረብ አልቻሉም።
ለሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀጥሮ የነበረው ችሎት ‘ፕላዝማው ተበላሽቷል’ በሚል ለዛሬ ሚያዝያ 15 ቀን ተዘዋውሮ ነበር።
በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል የተዋረድ ክርክር በማድረግም ያለ ብይን ጊዜው እየተጓተተ ይገኛል። ያለ አንዳች ብይን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱም የፍርድ ሂደቱን የማጓተቱ አካል ነው። ‘ዳኛ የለኝም፣ ፕላዝማ ተበላሸብኝ’ እያለ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚያደርገው ማጓተትም ከፍተኛውን ፍርድ ቤት እንደማገድ ይቆጠራል።