እንኳን ለ43ኛው የካራማራ የድል በዓል አደረሠን!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) እንኳን የሶማሌው ጀኔራል ዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር ድል ለተደረገበት 43ኛው የካራማራ የድል በዓል አደረሳችሁ እያለ በዓሉን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን በማስከበር ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባል። ከአድዋ እስከ ካራማራ በወርሃ የካቲት የምንዘክራቸው የድል በዓላት ዛሬም ሉዓላዊ ክብራችንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ምሳሌዎች ናቸው። በአባቶቻችን ዘመን ያልተደፈረች ኢትዮጵያ በእኛ ዘመን አትንበረከክም። ከተንበርካኪነት ዲፕሎማሲ ልንወጣ ይገባል። የአደግዳጊነት ታሪክ የለንም። በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንሥት ግብፅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ብትሞክርም አፄው በአባይ እንደሚጎዷት ገልፀው አደብ አስገዝተዋታል። በ1632 ዓ.ም. ፖርቹጋሎች ለወታደራዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ሆኖም ከመጡበት አላማ ውጭ የሀገራቸውን ሀይማኖት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ሲሠሩ ተደረሰባቸው። የወቅቱ መሪ አፄ ፋሲል ወዲያውኑ ከኢትዮጵያ ምድር አስፈተለኳቸው። ወቅቱም ‘በር የመዝጋት ዘመን’ እየተባለ ይጠራ ነበር።
ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አስረኛው የአብዮት በዓላቸውን ሲያከብሩ “በርከታ ገንዘብ አፍስሳችሁ ደግሳችኋል። ሀብት አባክናችኋል” የሚል ትችት ከተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች መጣባቸው። መንግሥቱም “በርገጥ በርካሽ ወጭ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሠርተናል። ነገር ግን ምን አይነት ኪችንና ሳሎን እንደምንገነባ እናንተን አናማክርም” በማለት ገድበዋቸዋል። የተጠቀሱት መሪዎች የመሪነት የውሃ ልክ ናቸው እያል አይደለም። የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር አንፃር ያደረጉት ተግባር ግን ይህ ትውልድ ሊወርሰው የሚገባ ነው።
በአዲሱ የጆ ባይደን አስተዳድር የሚመራው የአሜሪካ መንግሥት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ ያሳየው አጉራ ዘለል ጣልቃ ገብነት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ሳይጋበዝ ጓዳችን ውስጥ ገብቶ በውስጥ ጉዳያችን ከመወሰኑም በላይ እርስ በእርስ የሚከፋፍል ነው። በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል የወጣው መግለጫ አልፎ ተርፎ የአማራና የትግራይ ‘ክልሎችን’ የአስተዳድር ወሰን ለመቅደድ የዳዳው ሆኖ አግኝተነዋል። “የአማራ ሃይሎች ከትግራይ ይውጡ” የሚለው አገላለፅ የሚያንፀባርቀው ይህንኑ ነው። የአማራ ልዩ ሃይል የሚገኘው የራሱ የአማራው ሕዝብ አፅመ ርስት በሆኑት ወልቃይት፣ ጠለምትና ራያ ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ የእነኝህ አካባቢዎች አስተዳድር ወያኔ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ይተዳደሩበት ወደ ነበረው ግዛታቸው ተመልሰዋል። ኗሪዎች በርካታ አሥተዳድራዊ ጉዳዮችን የሚያስፈፅሙት ባሕር ዳር በሚገኘው የአማራ መስተዳድር ነው። በመሆኑም ትግራይ ውስጥ የከተመ የአማራ ወታደራዊ ሃይል የለም። የአማሪካ መንግሥት ወያኔ ቅብ የትግራይ ፅንፈኛ ብሔርተኞች እየተንከባለሉ የተነፈሱትን ከማስተጋባት ይልቅ እውነታውን ሊያገናዝብ ይገባል።
የተባለው ሆኖ ቢሆን እንኳን የኢትዮጵያን የጓዳ ድስት አሜሪካ የምታማስልበት አመክንዮ የለም። ሊኖርም አይገባም። ‘አማራ ከትግራይ ይውጣ፤ ትግራይ ከአማራ ይውጣ’ ማለት ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ውጭ እንደማለት ነው። ፓርቲያችን ለዚህ ቅጣንባር የለሽ ውሳኔ ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎት ያለው ከማለት ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በቅርቡ በማዕከላዊ መንግሥቱና በትግራይ መካከል ስላለው የወያኔን አማጺ ቡድን የማስወገድ እንቅስቃሴ ላይ ከኬንያው ፕሬዚደንት ጋር ተወያይተዋል። ይህም ከትንኮሳ ሌላ ስም ሊሰጠው አይችልም። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ማግኘት ያለባቸው የኢትዮጵያን መሪ እንጂ የኬንያን አልነበረም። በአፍሪካ ሕብረት በኩል ኬንያ የምታስፈልግበት አጀንዳ ቢኖር እንኳን ኢትዮጵያን ማነጋገር ይቀድማል። ኬንያና አሜሪካ በሚያደርጉት ውይይት ላይም ባለጉዳይዋ ሀገር ልትሳተፍ ይገባል።
አሜሪካ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡም ጠይቃለች። በቅድሚያ ወታደሮቹ ስለ መግባት አለመግባታቸው ተጨባጭ መረጃ ሊቀርብ ይገባል። ገብተውም ከሆነ ዋና ከተማቸውን አስመራን በሚሳኤል ለደበደበው የወያኔ አማጺ ቡድን ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ እናምናለን። ንፁሃን ትግሬዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ከሆነ ባልደራስ ይቃወማል። ሆኖም ግን ይህን ለመቃወምም ሆነ ከግዛቷ ለማስወጣት ኢትዮጵያ በቂ ነች። የአሜሪካ ድጋፍ አያስፈልጋትም። ኢትዮጵያ እስከፈለገች ድረስ የኤርትራንም፣ የሩሲያንም፣ የቱርክንም ጦር ሰራዊት ማስገባት ሉዓላዊ መብቷ ነው። ኢትዮጵያ ከፈለገች የኤርትራ ወታደሮችን ከማስገባትም በዘለለ ሰፊ የጦር ማዕከል ልትገነባላቸው ትችላለች። አሜሪካ ከወደደችው ሀገር ጋር የጦር ስምምነት ስትፈፅም ኢትዮጵያን እንደማታስፈቅደው ሁሉ ኢትዮጵያም ከወደደችው ሀገር ጋር የጦር ቃል ኪዳን ትዋዋላለች።
በኢትዮጵያ፤ ትግራይ የሚደረገው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ወያኔ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም ግምኛ ሥር ሰዶ የቆየ ነው። “የወያኔ ፖሊሶች አስገድደው ደፈሩን” በሚል የተንቤን ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው ይታወሳል። ሴት ልጅ ከባሏ ዓይን ስር በታጣቂ ሃይል ተገዳ ስትደፈር ኖራለች። ይህ መቆም አለበት። ከወያኔ በኋላም ቀጥሎ ከሆነ በገለልተኛ ተቋማት ተጠንቶ ተጨባጭ መረጃ ሊቀርብ ይገባል።
በአሜሪካ መንግሥት በኩል የቀረበው ግን የአንድ ወገን ጩኸትን ብቻ ያስተጋባ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እንዲሠራ ባልደራስ ያሳስባል። ካለፈው ጥቅምት መጨረሻ ማለትም ወያኔ ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ጦርነት ከከፈተበት ጊዜ ጀምሮ የሱዳን ወራሪ ሰራዊት ጓንግ ወንዝን ተሻግሮ ኢትዮጵያ ገብቷል። ይህ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል። ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነትም የአብይ አሕመድና የኢሳያስ አፈወርቂ የግል ሽርክና እንደሆነ ቀጥሏል። ስምምነቶች ለሁለቱም ሀገራት ሕዝቦች ግልፅ ተደርገው መንግሥታዊ ቅርፅ ሊይዙ ይገባል። በተጨማሪም አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ያሳስባል።
ድል ለዴሞክራሲ!