አወይ እኔነቴ (በቃሉ ሰውመሆን)
ጅምሬ ቀዳሚ
ጉዞዬ አድካሚ
ውጣ ውረድ ያለው
ከሚዛኑ ዝንፍ ወይፍንክች የሌለው
ከአፈር በቅዬ
በአፈር አብቅዬ
አፈር እየገፋው አፈር የሚገፋኝ
አፈር እየበላው አፈር የሚበላኝ
ማብቀያም ዘርም ነኝ
በአንድነቴ ውስጥ ህብረ-ቀለም ያለኝ
ሀዘኔን፣ ደስታዬን የምቋጭ በስንኝ
የዘመን ውዥምብር የማይሸረሽረኝ
ባቋሜ ጸንቼ በቃሌ የምገኝ
ሲጠልፉኝ አቅንቼ ሲገፉኝ የምሸኝ
ቀለምን ጠንቅቄ በቃሌ እምወጣ
ከምንጩ ቀድቼ ከምንጩ እምጠጣ
በሀሳብ ወጥኜ በምግባር ተስዬ በግብር የምወጣ
የተላለፈኝን አይቀጡ ምቀጣ
የተማመነኝን ፍቅር የማጠጣ
አወይ እኔነቴ
ከጥንቱ ቀድቼ የነገን ማስላቴ
የማይመነዘር ዝንጉርጉርነቴ
ምናቤ እምቅ ንግግሬ ቅኔ
በቀኙ ውዬ የማድር በጎኔ
መነሻዬ ብእር መቋጫው ምናኔ
እራሴው ቋጥሬ እራሴው ምፈታ
በጊዜ ማልቃኝ በስፍር በቦታ
በማለዳ አፍርቼ የምበስል ማታ
የሆንኩትን ሁኜ ያልሆንኩትን ያልሆንኩ
በጥበብ መጥቄ ሰማይን የታከኩ
በስጋ ቀጥኜ በመንፈስ የወፈርኩ
በትውልድ ቅብብል እየተሰናሰልኩ
ጥንቴንም ዛሬዬን ነገዬንም ያከልኩ
ፊደልን ጠንቅቄ በእውቀት የበሰልኩ
በምድር እየኖርኩ በሰማይ የነገሥኩ
የጽድቅ መንገዴን መድረሻዬን ያወኩ
መንጠላጠያዬን መሰላል የጨበጥኩ
ወድቆ አለመቅረትን ያወኩኝ ጠንቅቄ
ከቅርቡ እያደርኩኝ የማስብ አርቄ
በሀሳብ አቅርቤ በምናብ አርቄ
የሩቁን ከቅርቡ በውል ደባልቄ
በውዥንብር ዓለም የምገኝ ጠንቅቄ
የማመልክ በስሉስ
ከአጸዱ ውዬ የማድር ከመቅደስ
የምምል በማሪያም
አርማዬ ሶስት ቀለም
አወይ እኔነቴ ኢትዮጵያዊነቴ፡፡
(በቃሉ ሰውመሆን)