አኬልዳማዋ ኢትዮጵያ(ውቤ ደነቀው መኮንን)
ትሕነግ/ኢሕአዴግ ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ሀገራችንን ሊበላትና ሊበታትናት ሲሠራ ቆይቷል:: ሲያስገነጥል ውድ ታጋይ ልጆቿንም ቁም ስቅል ሲያሳይ የነበረው ይህ ቡድን በቆራጥ፣ ግንባራቸውንና ደረታቸውን ለሀገር ሲሉ ራሳቸውን ለጥይት የሰጡት ጀግና ከሕዝብ አብራክ የተገኙ የእማ ኢትዮጵያ ውድ ፍሬዎች በከፈሉት የህይዎትና የአካል መስዋዕትነት የተገረሰሰው ነውረኛና ሆዳም ቡድንን ተከላከልኩ ብሎ አዲስ ለመጣውና ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና ዴሞክራሲ ይወስዳል ተብሎ የተገመተው ራሱን የለውጥ ኃይል ብሎ የሰየመው ቡድን ወደ ሥልጣን ሲመጣ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ጨምሮ የብዙዎቻችን ደስታ እጥፍ ድርብ አድርጎት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው::
ይህ ኃይል ወደ ስልጣን ማማው በሚወጣበት ጊዜ ቲም ለማ ይባል፤ ቲም ገዱ ወይም ቲም ደመቀ፤ ዞሮ ዞሮ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ግምት ከ90% (ዘጠና እጅ ከመቶው) በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይሁንታና ድጋፍ ያገኘ እንደነበር የሚታወቅ እውነታ ነው::
ተረኛው ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የቡድኑ አምበል የሚያደርጓቸው የታሰበባቸው (calculated) ንግግሮች ለብዙዎች መሸንገል ምክንያቶች ነበሩ:: አሁንም እየተሸነገሉ ያሉ መኖራቸው ደግሞ ቡድኑ እስካሁን ካደረሳቸው የዜጎች ግድያ፣ መፈናቀል፣ መታገትና መሰል ችግሮች በበለጠ ወደ ፊት የሚመጣውን ችግርም አሳሳቢ ያደርገዋል:: እዚህ ላይ የአቶ ሽመልስ አብዲሳን የማደናገር ወይም ማሳመን (Confuse or Convince) አባባል ማሰብ የነገሮችን አካሄድ ግልጽ ያደርግልናል:: ለህዝባዊው ድጋፍ ምክንያት የነበሩትና ከተደረገው ዲስኩር አንጻር በሕዝብ ዘንድ ይፈፅሙልናል ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው ውስጥ፡-
- ከፋፋዩን፣ በታኙንና አፍራሹን የሀገሪቱ የበላይ ህግ ህገ መንግሥት ተብዬው የጠላት ማኒፌስቶና አንድን ቋንቋ ተናጋሪን በሙሉ ለማጥፋት በሰው በላዎቹ በትህነግና በኦነግ የተዘጋጀው እድሜው አእምሮ በሌላ ህዝባዊ ህገ መንግሥት ይተካል በሚል ተስፋ
- የፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር ቋንቋንና ዘርን ምርኩዝ ባደረገና በሕዝብ ምርጫና ፍላጎት መሠረት አዲስ የፌደራል መንግሥት አወቃቀር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተስፋ በማድረግ፣
- ከላይ ይደረጋሉ ተብለው የታሰቡ ለውጦችን መሠረት በማድረግ ነፃ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያከበረ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ስለታመነ፣
- ለዚህ ለተከናወነው ለውጥ በዋነኛነት ቀስቃሽና አቀጣጣይ የትግል ስልት በነበረው የማንነትና የውክልን ጥያቄዎች በአስቸኳይ እንደሚፈቱና ፍትሀዊ የውሳኔ እልባት እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት በመተማመንና በአጠቃላይ ተግባራዊ ይደረጉ የነበሩት ፀረ ሕዝብና ፀረ ዴሞክራሲ የሆኑት ህጎች ተወግደው ለመጨረሻ የተገረሰሱና ተመልሰው እንደማይተገበሩ በመተማመን ለአዲሱ የለውጥ ኃይል ነኝ ላለው መንግሥት ሙሉ ድጋፍ ተችሮት እንደነበር ሁላችንም በህሊናችን የቀረ የትናንት እውነት ነው::
በአንድ ሀገር የመንግሥት ለውጥ አስፈላጊ ሆኖ በሚከናወን ጊዜ ታግሎና መስዋዕትነት ከፍሎ ለውጡን ያመጣው ሕዝብ ይሁንታውን የሚሰጠው መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን ያለበት የሀገሩን ዳር ድንበርም የህዝቡን የዕለት ከእለት የፀጥታ ጉዳይ ማረጋገጫ ለነገ የማይባል ግዴታው እንደሆነ የታመነና ለአለማቀፋዊ እውነታ መሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም::
በዚህ አኳያ ሲቃኝ በመጀመሪያዎቹ የለውጥ ወራት በሀገራችን የሆነው ሁሉ ድንቅ ይመስል ነበር:: የሀገራችንን ውስጣዊ ሰላም ለማረጋገጥና ከውጭ ሊመጡ የሚችሉ በጎ ያልሆኑ ተጽዕኖዎችን ለማስቀረት ያለመ በሚመስል መልኩ ያኮረፈና የትጥቅ ትግል መሰል ትግል እናካሄዳለን የሚሉትን ኃይላት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አነስተኛና ከፍተኛ ቡድኖች ከያሉበት ጠርቶና ኤርትራ ድረስ የልዑካን ቡድን በመላክ ወደ ሀገር ቤት አስመጥቷል:: ሁሉም ግለሰቦች፣ ልዩነት አለኝ ብሎ በሀገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ቡድንና የፖለቲካ ድርጅት ቀጣዩን ትግል በሀገር ውስጥ በመሆን ሰላማዊና የአስተሳሰብ ትግል በማድረግ ብቻ ወደ ተፈለገበት አላማና ግብ መድረስ እንደሚቻልና የብረት ትግሉን አስወግደን ሀገራችን ኢትዮጵያን ሌሎች የለሙ ሀገራት ከደረሱበት የእድገት ደረጃ ለማድረስ እንድንተጋ ጥሪ ተላልፎ ከጎረቤት ሀገሮችም ጋር ፍፁም ሰላማዊና ትብብር የተሞላበት ግንኙነት ይኖረን ዘንድ አዲስ የተሰየመው የአብይ አህመድ መንግሥት ትጋትን ያሳዩ ይመስል ስለነበር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሕዝብ ድጋፍ አልተለያቸውም ነበር::
ሕልም እልም፤ ሕልም እልም!
አበው ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንዲሉ፣ የሰላሙን ጥሪ ተቀብለው ትጥቃቸውን ፈተው (እዚህ ላይ ትጥቅ ሳይፈቱም ከእነመሳሪያቸው የገቡም እንዳሉ ይታወቃል) ወደ ሀገር የገቡ በፊቱ የትህነግ/ ኢህአዴግ መንግሥት (ወሮ በላ ቡድን) ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደ ሀገር ቤት በደማቅ አቀባበል (እንዳንዶቹ እጅግ በተጋነነ የአቀባበል መስተንግዶ ጭምር ከገቡ በኋላ ግማሽ እንደ እንጀራ ልጅ ባለእጁን ጋባዥነትና ከፋይነት በባለ አምስት ኮከብ ሆቴል እንደሚንፈላሰስ መስማታችን ሳያንሰን ይኼው የባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ቅምጥል በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የመንግሥትን ስልጣን እቆጣጠራለሁ በሚል ቀቢፀ ተስፋ ምዕራብ ኢትዮጵያን የጦር አውድማ በማድረግ ከ20 (ሀያ) ያላነሱ የሕዝብና የመንግሥት ባንኮችን ያለማንም ከልካይና የተፈቀደ በሚመስል ውንብድና ዘረፈ:: አስዘረፈ::
የሀገር ያለህ፣ የመንግሥት ያለህ!!! ተባለ:: በወቅቱ ደራሽ አልነበረም ብቻ ላይን ሀይ ባይ በመጥፋቱ ያላስፈለገና ዘግናኝ አካል፣ የህይወትና የንብረት ውድመት መስዋዕትነት የምዕራብ ኢትዮጵያ ልጆች ከፈሉ:: ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሀነና ታለፈ የተረኝነቱ የመጀመሪ መጀመሪያ አትሉም?
ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘውና ቡራዩ ተብሎ በሚጠራው የከተማይቱ ክፍል ብሔርን በመሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ፣ እርድና የንብረት ውድመት እቃን በመሰባበር፣ማቃጠልና መዝረፍን ጨምሮ ሊካሄድ ያስተዋሉ የመሀል አዲስ አበባ ወጣቶች ድርጊቱን በመቃወም በሰላማዊ መንገድ ውቤ ደነቀው መኮንን አኬልዳማዋ ኢትዮጵያ ዳሰሳ 12 ቁጥር 03 ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሕዝብና ለመንግሥት ለማሳወቅ ሰልፍ ለወጡ ንፁሃን ወጣቶች ተመጣጠኝ ያልሆነ የአፀፋ እርምጃ ግድያን ጨምሮ የተወሰደ ሲሆን ለእስር የተዳረጉት ወጣቶች እስከአሁን ድረስ በእርስ እየማቀቁ እንደሆነ ይነገራል::
ከዚህ ከቡራዩ እልቂት ጀርባ ከነበሩት የሥውርና ረጅም እጃቸውን ካስገቡት የፅንፈኛ ቄሮ አባላት በተጨማሪ የፅንፈኛ ቄሮ አምበልና አዛዥ የአል ሐጂ በደል በካይ ወራሽ አልሐጂ ጀዋር መሀመድ እንደሆነ ቢታወቅም አሁንም ቄሱም መጽሐፉም ዝም ሆነላችሁ! ተረኝት ቁጥር ሁለት አትሉም ጎበዝ?
ከዚህ የቡራዩ የእልቂትና ማንነት መር የጅምላ ጭፍጨፋ ጥቂት ወራት ቆይቶ የፅንፈኛው ቄሮ አምበል ጀዋር መሐመድ ጥቃቶቹን አፏፋመ:: የደቡቧ ፈርጥ ወደ ሆነችው ውቧ አምባ (ሀዋሳ ጎራ ብሎ የኢጄቶም አምባል እኔው ነኝ በሚል መንፈስ እናንተ የክልልነት ጥያቄአችሁን አፋፍማችሁ ቀጥሉ መልስ ካላገኛችሁ በኃይል በመጠቀም ክልል እናደርጋችኋለን እናም ለ11/11/11 ቀጠሮ ሰጡና እስከዚያው የክልልነት ጥያቄአቸው ካልተፈፀም ጉድ ይወለዳል ብሎ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፎ መጣ::
ውድ እንባቢያን እደምታስታውሱት በ11/11/11 የተወለደው ከጉድም በላይ ነበር በዝርያ ሲዳማ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን እየተፈለጉና እየታደኑ በሀዋሳ ብቻ ላይሆን በአጎራባች ወረዳዎች ተጨፈጨፉ፣ በቤት ውስጥ እንዳሉ ሕፃናትና አረጋዊያን ሳይቀሩ ከነነፍሳቸው በእሳት እንዲጋፉ ተፈረደባቸው:: ሀብት ንብረታቸው ወደመ የተረፈውም ያለማንም ከልካይ ተዘረፈ አካላቸው ተጎድቶ ከሞት ያመለጡትም ተሰደዱ ተፈናቃይና ለማኝ እንዲሆኑ ተደረጉ::
ከሀዋሳው ሰቆቃ በግምት ከ3 ወራት በኋላ ለሚከበረው የኢረቻ በዓል አከባበር ውትወታ የተጀመረ በጣም ቀደም ብሎ ሲሆን ቅስቀሳውም የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ለየት የሚያደርገው ከአንድ መቶ ሀምሳ(150) ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ከተማ እንዳይከበር ተከልክሎ የነበረ በመሆኑና ዘንድሮ “ፊንፊኔ” በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበር መሆኑ አቦ ሽመልስ አብዲሳ እንደ ማስታወቂያ ሠራተኛ በተደጋጋሚና በተለያዩ ጊዜ በመናገር የስልጣናቸው ማዳበሪያ ያደረጉት ሲሆን ለማ መገርሳን በመተካት አዲስ ሹም ስለነበሩ የስልጣንና የመድረክ ሙቀቱን ግለቱን የተቋቋሙት አይመስሉም ነበር::
አይደረስ የለም የ2012 ዓ.ም የኢሬቻ በዓልም ደረሰና ከዋዜማው ጀምሮ የመዲናችን የአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች በትንሹ ከ5 ኪሎ ሜትር ራዲየስ (RADIOUS) ክርችም ተደርጎ የትራፊክ እንቅስቃሴ ከዜሮ በታች ሆኖ አደረ::
በዋዜማው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከካዛንቺስ አካባቢ እስከ መገናኛ ድረስ በትራንስፓርት እጦት መንገዱ በመዘጋቱም ምክንያት በእግር ጉዞ መሄዱን ያስታውሳል::
የበዓሉ እለት ማለትም የ2012 የኢሬቻ እለት ሀገሬ (አዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ) እቤቱ ቁጭ ብሎ በመዋል ሊከሰት ይችል የነበረውን ያላስፈላጊ ረብሻና ሊከፈል ይችል የነበረውን ያላስፈላጊ መስዋዕትነት በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ትዕግስት ቁጭ ብሎ በመዋል ታላቅነቱን አስመስክሯል ጨዋውና ወገን ወዳጁ አዲስ አበቤ::
የሥልጣ ትኩሳቱን ያልቻሉትና ነፍጠኛንና ነፍጠኝነትን የክብረ በዓሉ ማድመቂያና ማጣፈጫ ያደረጉት ኦቦ ሽመልሽ አብዲሳ በበዓሉ ዋዜማ መቸም የማይረሳላቸውና ነውረኛውን ዲስኩራቸውን እንዲህ ሲሉ አቅራርተው ነበር::
አጠቅላለሁ “ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ተከልክሎ የነበረውን ኢሬቻን በዓል በፊንፊኔ ስናከብር በተሰበርንበት ቦታ ነፍጠኛን ሰባብረነዋል እንዲሁም 150 ዓመት በኋላ የሀገሪቱን መዲና ተቆጣጥረነዋል!! አሉልኝ ታላቅ ጦርነት ድል አድርጎ እንደገባ የጦር ጄኔራል::
ከዚህ በኋላማ አዲዮስ ዴሞክራሲ፣ አዲዮስ አንድነት፣ አዲዮስ መደመር ተረኝነቱ አፍጥጦና አግጥጦ የለውጥ ኃይሉ መመሪያ እንደሆነና የአንድነት፣ እኩልነት የመደመር ሰበካው የተረኝቱ ጭምብል መሆኑ በይፋ ተገልጦ የታዩበት ሆኖ አለፈ::
የአብይ አህመድ የመደመር የፎቶ ሾው ፍልስፍና ሆነ የፓርክ ግምባታ ጭምብል እንዲሁም የቲም ለማ የኦሮሚያ ሪፖብሊክን የመመሥረት ድብቅ አጀንዳ በኦቦ ሽመልሽ የመድረክና የሥልጣን ሙቀት አለመቻልና መቃተት ራቁቱን ሆኖ ፀሐይ ይመታው ጀመረ::
የኢሬቻ በዓል አካባበር ሙቀት ሳይበርድ ምናልባትም ከአንድ ወር ባልበለጠ የጌዜ ርቀት ጉደኛ አጀንዳ ብቅ ያለ ሲሆን ይኸውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያሉትንና የተናገሩትን ሁሉ ያላንዳች ማንገራገርና ማወላወል ለሚቀበላቸው የትህነግ/ ኢህአዴግ ፓርላማ በመጠቀም ሀገራችን ለጉዳትና ለብጠብጥ ለሚዳርጉ ሰዎች ያለንት ትዕግስት አልቋል በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነና ከእኩይ ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን በማለት ካስጠነቀቁ በኋላ በማታው አውሮፕላን ወደ ሞስኮ እብስ አሉ ተባለና በማታው ዜና ሰማን::
ይህችን የጠቅላዩን ንግግር የሰማን ሁሉ ጎሽ ለካ ለካ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በጣም ትዕግስተኛ ስለሆኑ ነው እስካሁን የሖነው ሁሉ ሊሆን ዝም ያሉት::
ከአሁን በኋላ OMN ሰይጣናዊ መልእክት የሚያስተላልፍና ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ የሚያካሄድ ጽንፈኛ ሚዲያ (ቴሌቪዥን ስርጭት ይዘጋል ወይም የዚሁ ሚዲያ ባለቤት ጀዋር መሐመድ የተባለው ሰይጣዊ ሰው አደብ ይገዛል በሚል የእፎይታ ስሜት ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ተስፋ ሰነቀ::
ጠቅላዩ በዚያው ለፓርላማቸው ንግግር ባሰሙበት ቀን ምሽት ላይ ወደ ሞስኮ (ሩሲያ) መብረራቸው ከተሰማ ከጥቂት ሰዓታት ቆይታ በኋላ ንጉሠ ነገሥት አልሃጂ ጀዋር በካሳ በፌስ ቡክ ገፁ ተከብቤአለሁ ጥበቃዬም ተነስቶብኛል ቶሎ ድረሱልኝ በማት ለመናጆ መንጋው በማስተላለፍ ኡኡታውን አቀለጠዋል!!!
ከዚህ በኋለ የሆነውና የተፈፀመው እውን ይኼ ነገር እየተደረገ ያለው በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ስም ነው ወይስ ሌላ ቦታ በማለት የታየውንና የሚታየውን የግፍ ተግባር ማመን እስኪያቅት ድረስ የሰው ልጅ በብሔርና በእምነቱ እየተመረጡ እንደ ከብት ታረደ፣ ጭንቅላቱ በመንጋ ድንጋይ ተፈጠፈጠ፣ በቤት ውስጥ እንዳለ ከውጭ ተዘግቶበት ከእነነፍሱ በእሳት ላንቃ እንደ ጧፍ ተንቀለቀለ፣ የሰው ልጅ አስከሬን እየተጎተተ ፎቶግራፍ መነሻና መሳለቂያ ተደረገ፣ ከ80 ዓመት እድሜ ታማሚ አልጋ ቁራኛ ሽማግሌ እስከ የአራት አመት እድሜ ህፃን ላይ የሰው ልጅ ለእርድ ቀረበ እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ትዕይንት!!!
ከ3 እስከ 2 ተከታታይ ቀናት ይኸ ሰቆቃ ኦሮሚያ ተብሎ በተሰየመው በተለያዩ ቦታ ተከናውነ:: ጀዋር መሐመድም ፎከረም አቅራራም በመጨረሻም አሁን ያለንን አቅም፣ ጉልበትና ኃይል አሳይተናል አቁሙ ብሎ መንጋውን አዘዘ:: ንጉሠ ነገሥት ዘ- ቄሮ ወ- አራጅ አል ሃጂ ጃዋር መሀመድ ያዘዘው ሁሉ ሆነ::
ስለዚህ የጀዋር መሐመድ በዘርና በእምነት ለይቶ ንፁሐን ኢትዮጵያዊያንን ማሳረዱና አቅምና ጉልበቱን ያላየበትን ሁኔታ በማድረቅና ደስታና አጋርነታቸውን ለመግለፅ
- ኦቦ ሽመልስ አብዲሳን የቀደማቸው ያለ አይመስለኝም እሳቸውም አሉ፡- የጀዋር መሐመድን ጥበቃ ያነሳ በህግ ይጠየቃል ጀዋርን እንጠብቀዋለን እና ባስቸኳይ ጥበቃው እንዲመለስለት ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ ለማን? ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል (ለፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ) ይታያችሁ አንድ የክልል አስተዳደር የሐገሪቱን የፌዴራል ፓሊስ አዛዥ አሻቅበው ትእዛዝ ሲሰጡ ይህ እንግዲህ ከተረኝት እብሪት በስተቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል? “የድርጅቱ እናቲቱን አንቺ ልጅየውን አንቱ”
- ኦቦ ደውድ ኢብሣ (የዛሬን አያድርገውና ሳይንሳፈፍ በፊት)
- ኦቦ ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ እና ሌሎችም የተለያዩ ባለስልጣናት በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ የፓርቲ መሪዎች የእንኳን ደስ አለህ የአጋርነት መግለጫ በህብረት በዚያው በጀዋር OMN TV አስተላለፉ ጉድ ተባለ!!!
ይኼ ሁሉ የግፍ ግፍ ሲፈፀም በመሪ የሚያምነውና በመሪውም ተስፋ ያልቆረጠው ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባውን እያነባም እያበሰም አንዳች ነገር ከጠቅላዩ ይጠብቅ ነበር እንዳው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሁሉ ጉድ አልሰሙ ይሆን? ለሞስኮ ጉብኝታቸውን ዳሰሳ ቁጥር 03 ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. 13 አቋርጠው ይመጡና ሀገር ያረጋጋሉ ተብሎ ቢጠበቁ እሳቸው ምን በወጣቸው ቀስ ብለው፣ ዘንጠው ፎቷቸውን ተነስተው ስብሰባቸውን ጨርሰው እንኳን የ86 ንፁሃን ዜጎች ህይወትና ንብረታቸው (ይሄ ቁጥርር መንግሥት ባመነው መሠረት እንደሆነ ልብ ይሏል) የጠፋበት ሀገር መሪ ሊመስሉ አንድ ሰባራ ሳንቲም የጠፋበትም ነጋዴም አልመሰሉ ያልተነካ ግልግል ያውቃል አይደል ወጉስ!!!
ከሞስኮ ከተመለሱም በኋላ ከዛሬ ነገ መግለጫ ይሰጣሉ በፓርላማቸውም ፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባለሙት ንግግርና ለጀዋር መሀመድ በሰጡት ማስጠንቀቂያ መሠረትም ጀዋርን በቁጥጥር ስር አውለው ለህግ ያቀርባሉ ተብለ ሲጠበቁ እሳቸው እቴ!!! ወይ ንክች ያባቢለዋ ልጅ!!!
ለካስ ጀዋር መሀመድ የተፈቀደለት ወንጀለኛና ኢትዮጵያ ሀገራችንን ለመበተን ቡራኬ የተሰጠው አካይስት ኖሯል ወገን?
በግምት ከሞስኮ ከተመለሱ (ጠቅላዩ ማለት ነው) ከ10 ቀናት በኋላ ይመስለኛል በማንነታቸውና በሚያራምዱት እምነት ምክንያት እየተለዩ በምስራቅ፣ በደቡብ ምስራቅና የመአከላዊ ኢትዮጵያ ለተጨፈጨፉ አስከሬኖች ብሔርን ቁጥር በመስጠት በጉጉት ይጠበቅ የነበረውን መሪያዊ መግለጫ ውሃ በመቸለስ አይነት ኩም ካደረጉን በኋላ የጃዋር መሐመድ መንጋ በዋንኛነት በሰዎች አካልና ህይዎት እንዲሁም በንብረት ማውደምና አቢያተክርስቲያናትን በማቃጠል አደጋ ከደረሰበት የሀገራችን ክፍል ወደ ሐረር ከአጋር ባለሥልጣኖቻቸው ጋር በመሄድና ስብሰባ በመቀመጥ ጃዋር መሀመድ ወንድማችን ነው ለምን እንገለዋለን እስካሁን አብረን እየሠራን ነበር አሁንም አብረን እንሠራለን እንጠብቀውማለን በማለት ቢደሰኮሩልንና ጀዋር ኢስኮርታችን ነው ብለው ቁርጣችንን የነገሩንን በማሰብ ወደፊት የጨለማ ጊዜ እንደሚመጣና ትግሉ የመረረና የከረረ እንደሚሆን ነቢይ መሆን አላስፈለገንም ነበር::
ከዚያም ጊዜ በኋላና ያንን ሁኔታ ተከትሎ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉል ክልል ማንነትን መሠረት ያደረጉ እርዶችና የሰው ልጅ ደረትና ጭንቅላት የቀስት ጦር ማነጣጠሪያ እስኪሆን ድረስ በቁጥር ለሚታክት ጊዜ በተደጋጋሚ የሰው ህይዎት ሲቀስፍ የከረመበት ሁኔታ የትናንት ትዝታ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከዛሬ 1 ወር በፊት በሚሆን ጊዜ አቦ ሽመልስ አብዲሳና አቶ አሻድሊ ሀሰን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳደርን የአማራ ክልል ባለሥልጣናት የክብር ካባ ብለው ከሸለሙ ምናልባትም ከሽልማቱ 15 ቀናት በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው የመተከል ዞን (የቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር አንድ አውራጃ የነበረ መሆኑን ያጤናል) አስተዳደር አካላት በሆኑት የተለያዩ ወረዳዎች የአማራ/አገው ማንነት ባላቸው ነፃ በሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ በቀስት ወንጭፍና ዘመናዊ ትጥቅ በታጠቁ ወንበዴዎች ግድያ የንብረትና የቤት ቃጠሎ በተካሄደበት ወቅት የነፍሰጡር እናት ሆድ በሳንጃ ተቀዶ በማሕፀን ውስ የነበሩና ለመወለድ ጥቂት ጊዜ የሚቀራቸው ህፃናት ሜዳ ላይ ጫካ ውስጥ ተጥለው የታዩበትን ሁኔታ ወላድ ሁሉ ምን ሊል እንደሚችል ፍርዱን ለአንባቢ እተወዋለሁ::
እንግዲህ እኚህ የክልል አስተዳደር ናቸው ም/ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን መተከል ከጎበኙ በኋላ ህብረተሰቡ መንግሥት ይደርስልናል ብሎ መጠበቅ የለበትም:: ይልቅስ ራሱን አስታጥቆ አካባቢውንና ቤተሰቡን እንዲሁም ራሱን መከላከል ይገባዋል አሉ:: አቶ አሻድሊ ሀሰን ይክፉም ይልማ የሀገሪቱን ም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲተቹ የም/ጠ/ሚ/ውን ንግግር ከአንድ ከማይረባ ሰው የሚጠበቅ ንግግር አይነት እንደሆነና እኛ ከፈለግን “እነ አቶ አሻድሊ ሀሰን” በአንድ ቀን ድምጥማጡን ነው የምናጠፋው ማንን? አማራውንና አገውን ስለዚህ ብንከባበር ይሻላል በሚል ዛቻ አቶ ደመቀን አሻቅበው ያስጠነቀቁበት ሁኔታ አሁንም የፍንጅርቱ እናቲቱን አንቺ ልጅየውን አንቱ” ብሄል እንድናነሳ ያስገድደናል::
ይህ በአንዲህ እንዳለፈና ምናልባትም ከዚህ ትዕይንት ቀደም ብሎ በሀገራችን በደቡብ ክፍል የሚገኘው የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ አንስቶ ተግባራዊነቱን ለማፍጠን የአደባባይ ተቃውሞና የጥያቄው መልስ ይፈጥን ዘንድ ሰልፍ በወጡ ዜጎች ላይ የግድያና የአካል ማጉደል ርምጃ የተወለደበት ሁኔታ ሳንዘነጋ አሁን በዚህ ወቅት የዚህ ጽሑፍ እራቢ የታዘባቸውን ነገሮች በሚከት ትብብር ሁኔታ አሁንም በሀገራችን ደቡብ በሚገኘው የጉራ ፈረዳ ወረዳ ማንነትን መሠረትና ምርኩዝ ያደረገ ከላይ በተጠቀሱት አረመኔያዊ የአገዳደል የጭካኔ ስልት በመጠቀም አካባቢውን የዞን ደረጃ ለመስጠት የሚፈልጉ የታጠቁ ኃይላት (ሽኮዎች) ይላቸዋል:: ዜናው ንፁሐን ዜጎች እየተጨፈጨፉ ይገኛል::
መንግሥት እርምጃ ምን ይሆን? ይህን? የነፍስ አድን እርምጃ መውሰድ ይሆን? ወይስ አሁንም መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም ይሉ ይሆን::
ስለዚህ ይህች ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ለሰላም ወዳዱ ህዝቧ ላይን ለአምባገነንና ጨፍጫፊ መሬዎችና ጀሌዎቻቸው የገፀ በረከት የተሰጠች ሀገር እስከምትመስል ድረስ የሚተካኩት መሪዎች ሁሉ በተለይም ከሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሰባት ዓ.ም (1967) ወዲህ በኢትዮጵያ የቅዥት መንበር ላይ ፊጥ ያሉ መሪዎ የኃይማኖት መሪዎ የማይገደዷቸው፣ ሚኒስተሮቻቸው ተቃውሞ የማያቀርቡባቸው ይልቅ እጅ በመንሳትና ሲያስነሳላቸው ጭምር በማጨብጨብ በአምባገነንነት እብሪት እንዲያብጡ የሚያበረታቷቸው፣ በቅርብ ጓደኛ ምክር የማይሰማቸው ሲፈልጉ የሚበትኑት ሲፈልጉ የሚደምሩት ሕዝብና ሀገር ነው ለካ ያላቸው::
የካቢኔ ሚኒስትሮች የጠ/ሚው፣ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልሆነ የጠርና የጠርና የፀጥታ ኃላፊዎችም እንዲሁ የሾሚ አለቃቸው እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልሆኑ ሁሉ ሕዝብ በዘፈቀደ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ተጨፍጭፎ ሲያልቅና የሀገር ሀብትና ንብረት ሲወድም፣ ሀገር መስራች ብቻ ሳትሆን በራሷ ሀገር የሆነችና የብዙ የሀገር ውለታዎች ባለቤት የሆነችው እናት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስትደፈር፣ ስትቃጠል ስትወድም ዝም ብሎ ባልታዘዝኩም አባዜ ቆሞ የመመልከት ነውር እየተሰራባት ያለች ምናልባትም ከአምላክ በስተቀር ባለቤት የሌላት ሀገርና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብም በአላየሁም አልሰማሁም አውቆ አይን የመጨፈን ተንኮልና ይች ሀገር ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ (League of Nationes) የመጀመሪያውና የከሸፈው እንዲሁም በኢትዮጵያ ምክንያት የፈረሰው የንጉሠ ነገሥቱ የድረሱልኝ ጥሪ ውድቅ ያደረገበትና በኢትዮጵያና በወራሪው ኢጣሊያ ላይ እኩል የመሣሪያ ሽያጭ ማዕቀብ የጣለበት ክህደት::
በሁለተኛው ደረጃ በ1990 እ.ኢ.አ የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወራሪንና ተወራሪን በአንድ የተንኮል አይን በማየትና ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ በእነኸርማን ኮህን የተደረገብን አለማቀፋዊ ደባ ከዛሬ ሦስተኛው ደረጃ ከዛሬ ሦስት ዓመት ወዲህ፣ በዚህ ባለንበት ዘመንና በአሁኗ ሰዓት ጭምር ተከታዮችን እንዲሁም ቅድስት የተዋህዶ ቤተክርስቲንን ለይቶ ኢላማ በማድረግ በራሳችን መሪዎችና በጽንፈኞች ብሔርተኞች እየደረሰ ያለውን ስብአዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ውድመት ሊተባበሩት መንግሥት ጽ/ቤት ለተለያዩ ሰብዓዊ ጉዳይ ይመለከተናል ለሚሉ ዓለማቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሰላም ወዳዱ አለማቀፋዊ ህብረተሰብ በጀግናው የሕዝብ ልጅ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሆነው እንቁ ኢትዮጵያዊ በታላቁ እስክንድር ነጋ አማካኝነት ኢትዮጵያ ለመላው ዓለም ብታሳውቅም አሁንም በቸልታ በማዬትና እንደ ሩዋንዳ የሁቱና ቱትሲ ኢንተር ሀሞይ ፍጅት አስከሬን ሊቆጥሩ ይመጡ ይሆን? ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ የሚደርስላት የነገሥታት ንጉስ የአማልካቾች አምላክ ቸሩ መድኃኒያለም አይዘነጋትም አሁንም ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋና የህዝቧም እንባ ወደ አምላካቸው ጎርፍ ሆና ይፈስ ዘንድ ግድ የሚለን ጊዜ ላይ ነንና አምላካችን ይድረስልንና ፅናትና ጥንካሬውን ይቸረን ዘንድ ሁላችንም በአቋማችን እንፅና!!!
ንቁም በበህላዊነ እስከንረክቦ አምላክነ ያለውን የሊቀመላኩ ቅ/ገብርኤልን ጽናት ጥንካሬ ይስጠን።
ወስበሀት ለእግዚአብርሔር! አሜን (3)