ትብብሩ ለኢትዮጵያ ተስፋ ፤ ለአዲስ አበባ የህልውና ጉዳይ ነው !
የባልደራስ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ከቃሊቲ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ፤ በዛሬው ዕለት መጪው ሃገር አቀፍ ምርጫ በትብብር ለመስራት መስማማታችን ለህዝብ ይፋ ሆኗል ። ይህ ትብብር የአብን እና የባልደራስ ብቻ እንዳይሆን ፥ ባልደራስ ለባለፉቱ ወራት ይፋዊ ጥሪ ለፓርቲዎች በማቅረቡ ፤ በአዲስ አበባ ላይ የተጋረጠውን አደገኛ ችግር፤ በእኩል ለመጋፈጥ እና በዲሞክራስያዊ የምርጫ ሥርዓት፣ ለህዝብ ጠንካራ ተመራጭ ትብብር ለመፍጠር የተቻለንን ጥረት አድርገናል።
አሁንም ቢሆን አዲስ አበባን ለመታደግ ቁርጠኛ ፍላጎት ካላቸው ፣ በተለይ የልዩ ጥቅም ፍላጎት የማይቀበሉ ፣ አዲስ አበባ የኗሪዎች መሆኗን እና የኢትዮጵያዊያን መናገሻ ከተማ እንደሆነች በጽኑ ከሚያምኑ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ስለ አዲስ አበባ ለመምከር እና በጋራ ለመስራት ፤ ባልደራስ ከግማሽ መንገድ በላይ በመሄድ ከዚህ ቀደም ላቀረበው የአብረን እንስራ የትብብር ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል ።
በዛሬው ዕለት ፤የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ በጋራ ለመስራት ይፋዊ የትብብር ስምምነት መገለጡ ፤ትብብሩ ለኢትዮጵያ ተስፋ ፤ ለአዲስ አበባ የህልውና ጉዳይ ነው ! ይህ ትብብር እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የባልደራስ እና የአብን ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም ፣ ይህ ትብብር እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በአገር ውስጥ እና በውጪ የሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ላሳዩት ድጋፍ ፤ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ !
በተለይ በመጪው ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ፣ ለአዲስ አበባ የሚበጀውን ለመምረጥ የተግባር ሰው መሆን ግድ ነው።
አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያ ማዳን ነው !
ትብብር ለእውነተኛ ዴሞክራሲ !!
ድል ለዲሞክራሲ !!!