ብሄራዊ መግባባት ሽብር ባልፈጸመ ሰላማዊ ታጋይ ላይ የሽብር ክስ በመመስረት ህጉን የፖለቲካ ተገዥ በማድረግ አይገኝም!!!
“እውነት ከአንባገነኖች ክንድ ትበረታለች”!
እናት አገራችን ውዲቷ ኢትዮጵያ ከአያት ቅድም አያቶች አጥንት ፍላጭ ተማግራ፣ አፈሯ በደማቸው ተለዉሶ ተቦክቶና ተጋግሮ ለሺዎች ዘመን የቆመች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ነገዶች ባህል ከባህል፣ሃይማኖት ከሃይማኖት ነገድ ከነገድ ተስበጣጥሮ ያቆማት የውህድ ማንነት ተምሳሌት ሀገር ናት፡፡ ይህም በልጆቿ ተጋድሎ ለዘመናት ከውጭ ወራሪ ሀይል ተጠብቃ በመቆየት የጥቁር ህዝብ ፈርጥ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ሆኖም በልጆቿ አጥንትና ደም ራሷን ጠብቃ ብትቆይም በሃሰት የታሪክ ትርክት በገዢዎች መረን የለቀቀ የስልጣን ጥም ውስጣዊ አንድነቷን አስጠብቃ መቀጠል ከፍተኛ ተግዳሮት ሁኖባታል፡፡
የህወሓት/ኢህአዴግ የእንግዴ ልጅ ኦህዴድ/ብልጽግና መራሹ የዚህ ዘመን ተረኛ ገዢ ቡድን በዘመናት መከራና ተድላ ተጋምዶ የነበረውን ወደገደል እያንደረደረ፤ከዚህ ቀደም ከነበረው በባሰ ፍጥነት እየነጎደ እንደሆነ የሰሞኑ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው ‹‹የሽብር ክስ›› እና የፌዴሬሽልን ምክር ቤት ‹‹የትግራይ ክልል ምርጫ››ን አስመልክቶ በነሐሴ 30/2012 የወሰደው አቋም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ዶ/ር አብይ አህመድ በ2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን ‹‹ኢህአዴግ አሸባሪ ነው›› ለዚህም ያለፈውን ይቅርታ በመጠየቅ ለወደፊቱ እንደማይደገም፣ ለበደላቸውም እንደሚክሱ ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ የሁለት ዓመት የሥልጣን ጉዞአቸው የህዝብ ጥያቄን መፍታት ሲሳናቸው፤ ሌሎች የህዝብን ጥያቄ አደራጅተው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ሲታገሏቸው “ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህ “ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን” ዛቻ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ፣አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም፣ ወ/ት አስካል ደምሴ እና ሌሎች አባላት ላይ አሻሽለነዋል፣ በሽብር ህግ ስምም ህዝባችንን ስናሸብር ነበር ባሉት አዋጅ መከሰሳቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በእጅጉ አሳዝኖታል፡፡ ፓርቲያችን ለውጡ ሀዲዱን መሳቱን በተደጋጋሚ የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳ ቢገልጽም አሁን በመሪዎቻችን ላይ የተዘጋጀው የፈጠራ ክስ “ላም ባልዋለበት…” የሆነ የስርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የተለመደ እኩይ ተግባር እየከወኑ መሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በሌሎች አመራሮቻችን ላይ የተከፈተው የሀሰት ክስ በፍጹም መሪዎቻችንን የማይመጥናቸው ይልቁኑም በፓርቲያችን ውስጥ ባላቸው ጠንካራ ተሳትፎ የሰላማዊ ትግል አርበኝነታቸውን በደንብ ያስመሰከሩ ሰንደቆቻችን ናቸው፡፡ ይህ የኦህዴድ/ብልጽግና የፈጠራ ክስ ማንን ለማሸበር እንደተነሳና በአንጻሩም ከምንም አይነት ህገ-ወጥ ድርጊት እንደማይገታ አስመስክሯል። ይሁንና ይህ አይነት እርምጃ ፓርቲያችን ሲያካሂድ ከቆየው የተጠናከረ ስላማዊ ትግል እንደማይገታው እና ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአጽንዖት ለማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡
ኦህዴድ/ብልጽግና ሀገሪቱን በአግባቡ መምራት አቅቶት በቅርቡ ህወሓት በትግራይ ያደረገውን ምርጫ አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስተላለፈውን አቋም አሳፋሪ ሆኖ አግኝተነዋል። የፌዴሬሽን ም/ቤቱ “ምርጫ እንደተደረገ አይቆጠርም” የሚል አቋም መውስዱ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለመላው የአገራችን ሕዝቦች ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ ውሳኔው አገሪቱ እንድትከፈል የይለፍ ካርድ እንደሰጠ ይቆጠራል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ስህተት የገዢው ፓርቲ አመራሮች በህግም በታሪክም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሊያጤኑት ይገባል፡፡
የወላይታ ህዝብ “የክልል ልሁን” ጥያቄ ሲያነሳ የዞን አመራሩ “ያልተፈቀደ ስብሰባ” ሊያደርግ ነው ስለሆነም የመከላከያ ሰራዊቱ ማስቆም አለበት በሚል ተልካሻ ምክንያት ከ36 በላይ የንጹሀን ህይወት ተቀጥፏል። የወዳጅነት ፓርክ ምረቃ በሚል ሰበብ “ወታደራዊ ትርዒት” ሲያሳይ የነበረው “ጠንካራ” ሰራዊት ህገ-መንግስቱን አስከብራለሁ የሚል ሰራዊት የትግራይ ህዝብ በጫና ምርጫ አድርግ ሲባልና ህውሓት እንደፈለግሁ እሆናለሁ በማለት ያሻውን ሲያደርግ ይህንን መሳይ እኩይ ተግባር ለማስቆም መቀነቴን ጣልኩ የሚል ምክንያት በማቅረብ በዝምታ ሲያልፈው ተስተውሏል። የሻሸመኔውንም ሆነ በአካባቢው የነበረውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ “አልታዘዝኩም” በሚል ሹፈት ማለፉንም ልብ ይሏል፡፡ ባልደራስ ለተረኛ ገዢዎች መከላከያ ሠራዊት በከተማ መካከል መብለጭለጭና የገመድ መውጣትና መውረድ “ትርኢቱን” አቆይቶ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ገዳዮች እንደ ቱሪስት እየተመላለሱ የዜጎችን ህይወት በማንነታቸው ምክንያት ሲቀጥፉ ሃይ ማሰኘት የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ በአጽንኦት ሊያስገነዝብ ይወዳል፡፡ ይህን የዜጎችን ደህንነት በማንኛውም አካባቢ ማስጠበቅ የፖለቲካ አስተዳደር ሀሁ መሆኑኑ ለማስታወስ ተገደናል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት “እንዳልተደረገ ይቆጠራል” በሚል በቀላሉ ያለፈው ነገር ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፈይዳ የሌለው በድርድር ሰጥቶ የመቀበል መርህን ያላገናዘበ፣ በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ በሚገኙ የክልል መንግስታት መካከል መጥፎ ልምድን የሚተው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ይህም በስርዓቱ ሆን ተብሎ በሚመስል ቸልተኝነት ሀገሪቱ እየሄደችበት ያለውን መዳረሻው የማይታወቅ የቁልቁለት ጉዞ መጀመሩን ያመለክታል፡፡
በመጨረሻም ሀገሪቱን በቅጡ ማስተዳደር ከስልጣን በላይ ማሰብን የሚፈልግ ሁሉንም ህዝብ እና የፖለቲካ ፓርቲ በእኩል አይን ማየትን የሚጠይቅ እንደሆነ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያምናል። አሁን ኦህዴድ/ብልጽግና እየሄደበት ያለው “አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ” ጉዞ ለሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት የማያስገኝ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ ጥፋትም ለዘመናት ጸጸትና ቁጭት ከማትረፋችንና ዕርስ በርስ ከመወነጃጀላችን አስቀድመን ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ባልደራስ ይገነዘባል። ይሁንና ገዥ ፓርቲው ብሄራዊ መግባባት በሚል የጀመረውን ባልደራስን እና ሌሎች የሚመለከታችውን ወገኖች ያገለለ አካሄድ ብሄራዊ መግባባት ያስገኛል ብሎ አያምንም። ሂደቱ ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ ተወደደም ተጠላም በህግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። የውይይቶች አጀንዳም በገዥ ፓርቲውና ተቀራራቢ አመለካከት ባላችዉ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ተጻራሪ አመለካከት ባላቸው ፓርቲዎች ጭምር ሊነደፍ ይገባል። ውይይቱም ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በህግ እና ተዛማጅ ሙያዎች ታዋቂነትን ያተረፉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ሊሳተፉበት ይገባል የሚል እምነት አለን። ገዢው ፓርቲ አገር አክሳሪ የሆነ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማይመጥን ብልጣብልጥነቱን ወደ ጎን በመተው የሚደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች ለዘላቂው የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስትነት የሚያስቀጠሉ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የወረስናቸውን ሀሰተኛ እና የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን የሚያቃኑ፣ ህግን በፖለቲካ መሳሪያነት በመጠቀም ህወሓት ሲተገብረው የኖረውን ሰላማዊ ታጋዮችን በሽብር የመክሰስ ልምድ ሊቀር ይገባል ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡ በያዝነዉ አዲሱ ዓመት ፓርቲያችን የአሁን እና የመጪውን ትውልድ ህልውና በማስቀጠል የዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማዋለድ ጥሪ እያቀረበ ለሂደቱ መሳካትም ጠንክሮ እንደሚሰራ ይገልጻል። ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ሃይሎችና የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ለብሄራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሰሩ በድጋሚ ጥሪያችን እያቀረብን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለመላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡
ክሹፍ ፖለቲካዊ ውይይት፣ አገራዊ መግባባትን አይወልድም!!!
መንግስት ከሰሞኑ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚል የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት ከመረጣቸው /ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀልባቸው ከወደዳቸው/ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ንግግር ማድረጉን ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፖርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ተከታትሏል። በዚህም ጉዳይ ላይ ፓርቲያችን ተወያይቶ ተከታዩን ዕይታ እና አቋም ይዟል።
አገራችን ኢትዮጵያን፣ ወደ ብሔራዊ መግባባት እና ልማት ይወስዳታል ተብሎ በህዝባችን እምነት ተጥሎበት የነበረው ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ የጀመረው የለውጥ ሽግግር የመቀልበስ አደጋ አጋጥሞታል። ትናንት የነበርንበትን ሁኔታ የሚያስንቅ ተረኝነት እና የዜጎች ሰላም ማጣት ውስጥ ገብተናል። በዓለም ሶስተኛ ታላቋ የዲፕሎማት ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ ለሶስተኛ ጊዜ የህይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት ተጋልጣለች። ከትናንቱ ጉዳት ይልቅ የነገው ዕጣ ፈንታችን እጅግ ያሰጋናል። አገራችን በኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ ዘመን፣ ዜጎች በላባቸው ያፈሩትን ሃብት በጠራራ ፀሐይ የሚያጡበት፣ ሴቶች የሚደፈሩበት እና ወንዶች የሚታረዱበት የምድር ሲኦል መሆኗን እየታዘብን ነው።
ከዚህ አሳዛኝ፣ አገራዊ እንዲሁም ትውልዳዊ ምስቅልቅል ውስጥ እንዴት መውጣት እንዳለብን ራዕይ አልባ የሆኑት ገዢዎቻችን፣ ትናንት የትህነግ ሎሌ የነበሩ እና ዛሬ ደግሞ ከመንግስት የሚሰጣቸውን አበል ብቻ የሚያስቡ የፖለቲካ አመራሮችን ፊት ወንበር ላይ አስቀምጦ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የተያያዘው ድራማ፣ የሽግግሩ ትልቁ ቀልድ ሆኖ አግኝተነዋል።
መንግስት በሃሳብ ገበያ ተወዳድሮ እንደማያሸንፈው የተረዳውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን፣ ሕግ ማስከበር ተስኖት በአዲስ አበባ ከተማ ለደረሰው ጉዳት በፈጠራ ወንጀል ያለአንዳች ማስረጃ ተጠያቂ ለማድረግ አመራሮቹን እስር ቤት በመከርቸም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀልባቸው ከወደዳቸው ፓርቲዎች ጋር ብቻ ተሰብስቦ “ስለብሔራዊ መግባባት” ተወያየን መባሉ፣ ከመነሻው የከሸፈ ሂደት ሆኖ አግኝተነዋል። ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ልጆች መካከል ተለይቶ እንዳይሳተፍ መደረጉ፣ ዜጎች በማንነታቸው እና አመለካከታቸው ምክንያት በየቦታው በኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ የሚደርስባቸው መድሎ ነፀብራቅ ሆኖ አግኝቶታል። ከሂደቱ መገለላችን ለአገራችን ሰላሟ የሚጠቅም እርምጃ ቢሆን፣ ፓርቲያችን በደስታ የሚቀበለው በረከት አድርጎ ይቀበለው ነበር። ነገር ግን ከ10 ሚሊዩን በላይ የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ልብ ውስጥ ያለውን ፖርቲያችንን በማሰርም ሆነ በማሸማቀቅ፣ የከተማውን እና የአገራችንን ችግር መፍታት እንደማይቻል የመጣንበት ሂደት በራሱ ይመሰክራል።
በዚች አገር እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ከተፈለገ፣ መንግስት የሚፈልገውን፣ የመሪዎችን ፊት እያዩ አቋሙን ከሚደግሙ ቡድኖች ጋር ሳይሆን፣ እንደ ባልደራስ፣ ለአገራችን የሚያስፈልገውን አማራጭ ከያዙ የህዝብ ድርጅቶች ጋር ለመነጋገር መንግስት ወኔው እና ቁርጠኝነቱ ሊኖረው ይገባል።
ከመጀመሪያውም፣ ብሔራዊ መግባባትን አጀንዳው አድርጎ የተነሳው ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ ከምርጫ በፊት እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ሊቀድም እንደሚገባ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ አሁንም ለአገራችን የሚሻለው አማራጭ፣ በሃሳብ ከሚለዩን እና ከማንወዳቸው ኃይሎች ጋር ቢሆንም፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ተነጋግሮ መግባባት ከመድረስ ውጪ አቋራጭ የሰላም መንገድ እንደሌለ ፓርቲያችን አበክሮ ያሳስባል። ብዙ ዋጋም ተከፍሎ ቢሆን፣ ዞረን ዞረን የምንመጣው ወደ ድርድር መሆኑን አበክረን እንረዳለን፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አገራችን ከገባችበት ከፍተኛ ግጭት እና የፖለቲካ ውጥረት እንድትወጣ ከብሔራዊ መግባባት ውጪ አቋራጭ መንገድ የሌለ መሆኑን በመረዳት ተከታዩን ምክረ ሃሳብ ለመንግስት እና ለተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ያቀርባል፣
1ኛ. ከብሔራዊ መግባባቱ በፊት ካለማስረጃ የተያዙት የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና የፓርቲው አባል የሆነው ገነነው አበራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣
2ኛ. በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በቀኝም ሆነ በግራ የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ያሉ ህዝብ የሚደግፋቸው የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ጥሪ ተደርጎላቸው የውይይቱ አካል እንዲሆኑ፣
3ኛ. ጉዳዩ የሚያገባቸው የሲቪክ ማህበራት እና የኃይማኖት አባቶች የሂደቱ አካል እንዲሆኑ ጥሪ እንዲደረግላቸው።
ከዚህ በተረፈ ግን መንግስት አሁን በያዘው አካሄድ እቀጥልበታለሁ የሚል ከሆነ፣ በአገራችን እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ካለማምጣቱም ባሻገር፣ ያለውን ፖለቲካዊም ሆነ የደህንነት ውጥረት የበለጠ እያባባሰው የሚሄድ መሆኑን ፓርቲያችን ማስገንዘብ ይወዳል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ
ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ