ባልደራስ በአዲስ አበባ ደረጃ ያዘጋጀውን የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ !!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በዛሬው ዕለት በራዲሰን ብሉ ሆቴል “አዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር እናደርጋታለን ! ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ደራጃ የተዘጋጀውን ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶ 120 ገፆች ያሉትና በ2 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። የአዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶቿን በ19 ንዑስ ምዕራፎች በዝርዝር በማስቀመጥ ፤ ለእነኚህ ተግዳሮቶች አበይት የችግር መፍቻ አማራጭ ፖሊስ በ28 ንዑስ ምዕራፎች በዝርዝር በማስቀመጥ ፤ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች የተሻሉ አማራጮችን በሰፊው የዳሰሰ ነው።
ባልደራስ የመጪውን ምርጫ የሚያሸንፍ ከሆነ ማሻሻያ የሚያደርግባቸውን ዋና ዋና ተግባራት እና የመፍትኄ አቅጣጫዎች በማኒፌስቶ በዝርዝር ተቀምጠዋል ።
አዲስ አበባን በተመለከተ፤ አዲስ አበባ ራስ ገዝ እንድትሆን እና በራሷ ልጆች እንድትመራ ባልደራስ ከሕዝብ ጋር በመሆኑ እስከመጨረሻው እንደሚታገለ ገልጿል፡፡ በመርኃግብሩ ላይ የባልደራስ የህዝብ እንደራሴ የተወካዮች ም/ቤት እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተገኝተዋል ።
የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ መድረኩን የመሩት ሲሆን ፤ የአደረጃጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢ/ር ጌታነህ ባልቻ የአዲስ አባባ የመሰረተ ልማት ጉዳይ በተመለከተ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ፤ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳምሶን ገረመው የአዲስ አበባ ሕጋዊና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች እና የፖሊስ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል ።