ባልደራስ በአዲስ አበባ ደረጃ የተቋቋመ የመጀመሪያው ‘ክልላዊ’ የፖለቲካ ፓርቲ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ቀኝ ዘመም (Center to right) ፓርቲም ነው። ባልደራስ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀቀኛው ጋዜጠኛ እና በፅኑው የሰብዓዊ መብቶች ታጋይ በአቶ እስክንድር ነጋ መሪነት በጎዳና ላይ ተመሰረተ። የግል ኩባንያ ከሆነው ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል በዘጠና ሺህ ብር የተከራየውን የስብሰባ አዳራሽ በአምባገነኑ መንግሥት ተከልክሎ ጎዳና ላይ ቅድመ መሥራች ጉባኤውን በማድረግ አቶ እስክንድር ነጋን ፕሬዚደንቱ አድርጎ መርጦ ተቋቋመ።
ቀጥሎም የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ.ኢ.አ.ድ.) ዋና ፅህፈት ቤት በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ እስክንድር ነጋ በቃለ መሀላ ስነ ስርዓት መሪነታቸውን ተቀብለዋል። የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትም ተመርጠዋል። ለዚህ ፓርቲ መሰረቱ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባልደራስ አዳራሽ የተመሠረተው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ነው። ባለ አደራ ምክር ቤቱ አላማው የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ሳይሆን ፖለቲካውን የሚገራ የሲቪክ ተቋም ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም በመንግሥት ክልከላ ሳይሳካ ቀርቷል። ከዚያም ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት መጣ።
በባልደራስ እምነት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይባላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ባለሙሉ ሥልጣን ነው። ሀገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን ከሕዝብ ይመነጫል። ባልደራስ ፕሬዚደንታዊ የመንግሥት አወቃቀር እንዲኖር ይታገላል። በፌዴራል መንግሥቱ ሥር የክፍላተ ሀገር መሥተዳድሮች እንዲኖሩም ይሻል። አብዛኛው የሥልጣን ክፍፍል ለፌዴራል መንግሥቱ መሰጠት አንዳለበት ያምናል። አዲስ በሚዘጋጀው ሕገ መንግሥትም የክፍለ ሀገር መስተዳድሮች ላይ የፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን የበላይነት እንዳለው ሊደነገግ ይገባል።
በኢትዮጵ ብቸኛው የሉዓላዊነት ባለቤት የፌዴራል መንግሥቱ ነው። ክፍላተ ሀገር (ኦሕዴድ/ብልፅግና ክልል የሚላቸው) ከመስተዳድርነት የዘለለ ሥልጣን ሊኖራቸው እንደማይገባ ባልደራስ ያምናል። ለዚህም እየታገለ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ባልደራስ የአዲስ አበባ ኗሪዎች የመኖሪያ ቤት እና የከተማ መሬት ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ያምናል። መሬት የመንግሥት መሆኑ ቀርቶ የዜጎች መሆን አለበት።
ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ሊሆን ይገባል። ለዚህም ፓርቲው እየታገለ ነው። የአዲስ አበባ ኗሪዎች ሁሉ እኩል ናቸው። በአዲስ አበባ ላይ ማንኛውም አካል ልዩ ጥቅም ሊኖረው አይገባም። ከተማችን ራስ ገዝ እንድትሆን ባልደራስ ይታገላል። ፓርቲው ሀብትን ከማከፋፈል ይልቅ ሀብት መፍጠር ላይ ያተኮረ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ያምናል። ለዚህም የግሉን ክፍለ ምጣኔ ሃብት ማጠናከር ያስፈልጋል። ኦ.ነ.ግ. እና ሕ.ወ.ሓ.ት. ሰራሹን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ ሂደት መናድ፣ አባቶች ያወረሱንን ታሪክና ቅርስ ተንከባክቦ ማስቀጠል፣ ፍትሕና ዴሞክራሲን ማስፈን፣ እምነትን መጠበቅ፣ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአንክሮ የሚታገልባቸው አምዶች ናቸው።