ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሆነ!!!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የአገር አቀፍ ፓርቲነት የእውቅና ሠርቲፊኬት ሰጠ፡፡
ባልደራስ ፓርቲ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት የሀገር አቀፍ ፓርቲነት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬትን 27/12/2016 ዓ.ም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረከቡን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምርጫ ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ- ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 64 1/ሀ መሰረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት ሊመዘገብ የሚችለው አስር ሺህ መስራች አባላት ሲኖሩት እና ከመስራች አባላቱ መካከል 40 ከመቶ የማይበልጡት የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች ሲሆኑ ነው፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ክልላዊ ፓርቲነት በተመዘገበበት ጊዜ ከአራት ሺሕ በላይ መስራች አባላትን ይዞ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
በአዋጁ መሠረት ባልደራስ ከክልላዊ ፓርተነት ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ለመሸጋገር በአራት ክልልሎች የ #ስድስት_ሺህ መስራች አባላት ፊርማን ማቅረብ ሲገባው፣ ፓርቲያችን ግን በስድስት ተጨማሪ ክልሎች ከ #አስር_ሺህ በላይ የመስራች አባላት ፊርማን በማሰባሰብ በአጠቃላይ ከ14 ሺሕ በላይ የመስራች አባላት ፊርማን በማስገባት የሀገር አቀፍ ፓርቲነት ሰርቲፍኬቱን ተረክቧል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በክልል አቀፍ ፓርቲነት ከተመዘገበበት 21/6/2012 ዓ.ም ጀምሮ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ባልደራስ ለአውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ እንዲመዘገብ አስተዋፅዖኦ ላበረከቱ አባላት እና አካላት በሙሉ የከበረ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡