በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ለየካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ ጉዳዩን በዋነኛነት የያዘው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አስቀድሞ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ፦ የምስክር አቀራረብ ሒደት ላይ ፤ ለምስክሮች ደሕንነት ሲባል በምስክር ጥበቃ አዋጁ መሰረት በዝግ ችሎትና ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡ ይፈቀድልኝ ሲል ፤ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓታል ።
በዚህም መሰረት ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን አቅርቦ እንዲያሰማ ቀጠሮ በተሰጠበት ቀን ፤ ዐቃቤ ሕግ ከጠቅላይ ፍ/ቤት እግድ ይዞ በመቅረብ የምስክሮች አቀራረብ በተመለከተ ይግባኝ የጠየኩ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እስኪ ሰጠ ተለዋዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት ያመለከተ ሲሆን ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የእግዱ ውሳኔ በመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት ጠቅላይ ፍ/ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ በማጽናት ፣ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በግልጽ ችሎት እንዲያሰማ እና የእግድ ትዕዛዝ በመሻር ፣ የዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ውድቅ አድርጓል ።
ዐቃቤ ሕግ በከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲሁም በጠቅላይ ፍ/ቤት ውድቅ የሆነበትን ይግባኝ ፤ ለፌዴራል ጠቅላይ ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ጠይቋል። ሰበር ሰሚ የቀረበለትን ይግባኝ ተመልከት ፤ ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አከራክሩ ይወስን በማለት ፤ መልሶ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት መርቶታል።
ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ላይ እንዳለ ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ቀደም በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት ፣ እነ እስክንደር በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፤ ፍ/ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ምስክሮች ለመስማት የተቀጠረ መሆኑን በመግለጽ ፤ በቅድሚያ በጠቅላይ ፍ/ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ በተመለከተ ግራና ቀኝ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ፍ/ቤቱ የጠየቀ ሲሆን ፤ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በጠየኩበት የምስክሮች አቀራረብ ላይ በነገው እለት የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ፍ/ቤት ቀጠሮ የተሰጠ በመሆኑ ጉዳዩ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ተለዋዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት ለፍ/ቤቱ ጥያቄውን አቅርቧል ።
የእነ እስክንድር ጠበቆች ለዐቃቤ ህግ በሰጡት ምላሽ ፤ ዐቃቤ ህግ የመጀመሪያው ጥያቄ በዚሁ ፍ/ቤት ውድቅ ሆኖበታል ፣ በጠቅላይ ፍ/ቤት በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም ። ጉዳዩን በመጨረሻም ጠቅላይ ሰበር ሰሚ ችሎት ዐቃቤ ሕግ ይዞ ቢቀርብም ፤ ሰበር ሰሚ ችሎት ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት መርቶታል።
ይሁን እንጂ በነገው እለት ቀጠሮ ስለ መኖሩ ደንበኞቻችን እንዲሁም እኛ የምናውቀው ነገር የለም ። መጥሪያ አልደረሰንም ። ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን በግልጽ ማቅረብ አልቻለም ።
በዚህ መሐል ደንበኞቻችን ያለ አግባብ በእስር ላይ ይገኛሉ ፤ ይህም በመሆኑ ፍ/ቤት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ስለ ሆነ ደንበኞቻችን ከእስር ሊለቀቁ ይገባል። ከጠቅላይ ፍ/ቤት መጠሪያ ሲቀርብ ደንበኞቻችን የቀረበባቸውን ክስ ከእስር ቤት ውጪ ሆነው መከራከር ይችላሉ። በማለት የእነ እስክንድር ጠበቆች ለዐቃቤ ሕግ ምላሽ በመስጠት የህግ ክርክር አድርገዋል ።
ግራና ቀኝ የህግ ክርክር የሰማው ከፍተኛው ፍ/ቤት ፤ ይህ ችሎት በጀመረው ሥራ ይቀጥላል ። አስቀድመን የሰጠነው ውሳኔ አለ ፤ ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን በግልጽ ችሎት አቅርቦ ያስመስክር። እስካሁን ድረሰ ለዚህ ችሎች የቀረበ እግድም ሆነ የተለየ ትዕዛዝ አልደረሰም ፤ ይህም በመሆኑ እኛ ሥራችንን እንቀጥላለን ። በማለት ለየካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጠዋት 3:30 ላይ ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ይዞ ይቅረብ በማለት ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፤ ዐቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቄበታለው ባለው ጉዳይ በነገው እለት የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ፍ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ቀጠሮ መኖሩን ገልጸዋል ። ሆኖም ግን የነገው ቀጠሮ በተመለከተ እነ እስክንድር የደረሳቸው ምንም አይነት መጥሪያ አለመኖሩን በችሎት ተገልጿል ።