በአፍራሾቿ ዶማ ላይ የተኛችው አዲስ አበባ (ጌጥዬ ያለው)
አንድ ተረት አለ፤ ትዝ የሚለኝ፡፡ ሁለት ወንዶች በአውድማ ተኝተው ነው፡፡ በውድቅት ሌሊት ጅብ መጣና የአንደኛውን እግር እንደሸንኮራ አገዳ ሞሽልቆ መቆርጠም ጀመረ፡፡ ጓደኛው ድምፅ ሰምቶ ምን እየሆነ እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡ ፈሪው ጓድ ‹‹ጅብ ነው፡፡ ተወው እግሬን ብቻ ነው የሚበላው›› አለው ነው ተረቱ፡፡ ‹‹ታዲያ እግርህን ከበላው ነፍስህንም እንዳይበላት ይሆን የምትጨነቀው?›› በማለት ጅቡን አባረረው፡፡ ፈሪውም አንካሳ ሆኖ ቀረ፡፡
በሰሞኑ የአቶ ሽመልሽ አብዲሳ ንግግር ላይ ‹የግለሰብ ኃሳብ ነው›፣ ‹የፓርቲው አቋም አይደለም›፣ ‹ንግግሩ ከመድረክ ዲስኩር አያልፍም› የሚሉ ማስተባበያወችን ስሰማ ነው እንግዲህ የፈሪው አንካሳ ታሪክ ትዝ ያለኝ፡፡ ሰሞኑን ይፋ የሆነው ኃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩት አይደለም፡፡ ከአስር ወራት በፊት ኢሬቻን ባከበሩበት ጊዜ በአደባባይ የተናገሩትም በይዘት ከዚህኛው የሚለይ አይደለም፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ ቁርጡን ነግረውናል፡፡ የከተማዋን የሕዝብ ስብጥር ለመቀየር እየሠሩ እንደሆነ የአቶ ለማ መገርሳን ንግግር ደግመውታል፡፡ ንግግሩ ወደ ተግባር ተቀይሮ ነው የመጣው፡፡ በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ የኦሮሞ ተወላጆችን ወደ ከተማዋ እያስገቡ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ አቶ ሽመልስ ያልገለፁት ሕገ ወጥ ሰው የማስገቢያ መንገዶቹ ምን ምንድን እነደሆኑ ነው፡፡ በሕገ ወጥ ሂደት ባለፉት ሁለት ዓመታት 5 ሺህ 9 መቶ የኦሮምኛ አስተማሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከተማዋ በመቶ አመታት ታሪኳ ያሏት መምህራን ከ40 ሺህ አይበልጡም፡፡ በዚህ ፍጥነት ከቀጠሉ በምዕተ ዐመቱ ውስጥ ከ295 ሺህ በላይ መምህራንን ያስገባሉ፡፡
‹የልማት ተነሽ አርሶ አደር ልጆች› የተሰኘው ፕሮጀክት ሌላኛው ሕገ ወጥ መንገድ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶችን በአዲስ አበባ የመሬት ባለቤት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ‹የከተማ ግብርና› የሚሉት ፕሮጀክትም አለ፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሞ ገበሬዎች ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው፡፡ አቶ ታከለ ኡማ ለእነኝህ ገበሬዎች በቅርቡ ትራክተር በነፍስ ወከፍ አድለዋል፡፡ የግብርና ቢሮ የሌላት የአዲስ አበባ የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት እንኳንስ ለትራክተር ለአንድ ማጭድ መግዣ በጀት እንዳላፀደቀ ግልፅ ነው፡፡ ገበሬዎቹ ‹አንዱ ሲበላሽ በሌላኛው እንድንሰራ ሁለት እና ከዚያ በላይ ይሁንልን› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በአንፃሩ በተመሳሳይ የእርሻ ዘመን በጎጃም የቢቡኝ ወረዳ ገበሬዎች ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በሽያጭም ቢሆን መንግሥት በወቅቱ እንዳላቀረበላቸው ገልፀዋል፡፡ የሚቀርብም ሲሆን ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ተማረው ከአዲስ አበባ – ደብረ ማርቆስ – ባሕር ዳር – ጎንደር – ሁመራ ድረስ የሚዘልቀውን ሀገር አቋራጭ የመኪና መንገድ በመዝጋት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡ ‹የከተማ ግብርና› ፕሮጀክት አዲስ አበባን የማትረባ ማለትም ለኑሮም ሆነ ለሥራ እምብዛም የማትፈለግ ለማድረግ ያግዛል፡፡ ይህንን በተመለከተ የአቶ ሽመለስ አብዲሳ፤ የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ንግግር ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ ማለትም ባለፈው ግንቦት መጀመሪያ በኢትዮጲስ ጋዜጣ ያሰፈርኩትን ሀተታ ቀንጭቤ እዚህም ላይ ልጥቀስ፡-
አዲስ አበባን እንደ በራራ
የከተማ ግብርና የረዥም ጊዜ እቅዱ አዲስ አበባን ማጥፋት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በርካታ ወጣቶች በየጊዜው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ ምክንያቱም ለተማረው ወጣት የተሻለ የሥራ ዕድል ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ ነግዶም ሆነ ተቀጥሮ አዲስ አበባ መኖር የተሻለ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ወጣት ወደ ከተማዋ የሚገባው በግብርና ዘርፍ የሥራ እድል እንዲፈጠርለት አይመስለኝም፡፡ ግብርናው ለዘመናት ሲሠራበት ቆይቶ በድካሙ ልክ ገበሬውን አልጠቀመም፡፡ ብዙዎች የሚማሩትም ከግብርና የተለየ (እነርሱ የተሻለ ይሉታል) ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ የተጀመረው የግብርና ፕሮጀክት በጓሮ አትክልት ደረጃ የሚወሰድ ፕሮጀክት አይደለም፡፡ በርግጥ ወደ ሰማይ ካልሆነ በቀር ወደ ጎን መስፋት ለተከለከለች ከተማ ጓሮስ የት ሲገኝ ነው፤ ከተማውን በሙሉ የገበሬ መንደር ሊያደርግ የሚችል ጅምር ነው፡፡ ለዚህም ነው በከንቲባና በሚንስትር ደረጃ እየተመራ ያለው፡፡ ፕሮጀክቱ ቤተ መንግሥቱ ውስጥም ገብቷል፡፡
ይህ ወደ ፊት ከተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ዜጎችን ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰው ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ከግብርና ወጥቶ ገበሬ ለመሆን ለምን ይመጣል? ለግብርና የተሻለው ቦታ እኮ ያደገበት ገጠሩ ነው፡፡ ‹ከተዋበው፣ ከተሞናሞነው፣ ትውልዴ ገጠርነው›ን እየዘፈነ በዚያው መሥራት ይችላል፡፡ ከተማ አስተዳድሩ የሌለን ግብርና አዲስ አበባ ላይ ከሚፈልግ ለምን ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ አላገዘም? ስለ ኢንዱስትሪ ሲያወራ የማይሰማው ለምንድን ነው?
የከተማ ግብርና ወደ አዲስ አበባ የሚገባውን ሰርቶ አዳሪ በመቀነስ የከተማዋን ዕድገት እንዲገታ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ‹አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ ነው ያረፈችው› ለሚሉት የኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ከነከተማነቷ ለመውሰድ የሚያደርጉት ጥረት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ተሞክሮ እስከ አሁን ስላልተሳካ ቀስ በቀስ ባለችበት ማጥፋት ነው ፍላጎታቸው፡፡ ይህንን ነው አቶ ሽመልስ ‹የማትረባ ከተማ እናደርጋታለን› ያሉት፡፡
አዲስ አበባ ታላቅ ከተማ ነች፡፡ ከኒዮርክና ከጀኔቫ ቀጥሎ የተባበሩት መንግሥታት ሦስተኛ መቀመጫ ነች፡፡ የአፍሪካ ፖለቲካዊ መዲና ነች፡፡ ይችን ከተማ አንዱን ቤቱን እያፈረሱ በማባረር፣ ሌላውን ከገጠር አምጥቶ የእርሻ ማሳ በመስጠት፣ ከ200 በላይ የጉልበት ሰራተኞችን በአውቶብስ ጭኖ ባሕር ዳር በመበተን እንዴት ትጠፋለች? እነ ታከለ ከባድ የቤት ሥራ የጀመሩ ይመሥላል፡፡ ግን ደግሞ በዓለም ላይ ብዙ ታላላቅ ከተሞች ጠፍተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም የአዲስ አበባን ያህል ካደጉ በኋላ ባይሆንም ከተሞች ጠፍተዋል፡፡
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነን ራሷ ቀዳሚት አዲስ አበባ ነች፡፡ ጥንታዊቷ የአፄ ዳዊት ከተማ በራራ ማለቴ ነው፤ በራራ የዛሬው አዲስ አበባ አካባቢ የበረች ሲሆን አማራዎች፣ ጉራጌዎች፣ ጋፋቶችና ማያዎች ይኖሩባት እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ ለከተማዋ መጥፋት ምክንያት ከሆኑት መካከል የኦሮሞ ወረራና የግራኝ አሕመድ ዘመቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ኦሮሞዎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ጀምሮ ከብቶቻቸውን ይዘው የተሻለ ውሃና ግጦሽ ወዳለበት አካባቢ ሁሉ ይፈልሱ ነበር፡፡ ጥያቄያቸውም ለከብቶቻቸው ሳርና ውሃ ነው፡፡ ይህም ለከተሜነት ፀር ነበር የሚል ነው የታሪክ ሀቁ፡፡ በወቅቱ በራራ የውጭ ሀገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን ነገስታት የሚኖሩባት ከተማ ነበረች፡፡ እንደ አክሱም፣ ጎንደርና ዛግዌ መናገሻ እንደነበርችም ታሪክ ያወሳል፡፡ የታከለ ኡማ የከተማ ግብርና ፕሮጀክት አዲስ አበባን እንደበራራ እንዳያጠፋት፤ ባያጠፋትም እንኳን እድገቷን እንዳያቀጭጭ መጠርጠር ስህተት አይሆንም፡፡
የፌዴራል መንግሥቱን መቀመጫ መንሳት
እንደ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር ሌላኛው አዲስ አበባን የማጥፊያ መንገድ የፌዴራሉን መንግሥት መቀመጫ በሦስት ወይም አራት ከተሞች ላይ ማድረ
GtyeBald, [18.06.21 08:48]
ግ ነው፡፡ ይህ የሽመልስ ንግግር ብቻ አይደለም፡፡ የኦሕዴድ/ብልፅግና አቋም ብቻም አይደለም፡፡ ከአመታት በፊት ፀጋዬ አራርሳ ‹አዲስ ስታንዳርድ› በተሰኜ ገፀ ድር ላይ ይህንኑ ሃሳብ ጠቁሟል፡፡ ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኞች በየቃለ መጠይቆቻቸው እንደ ታላቅ ሳይንሳዊ ግኝት ቆጥረው ለከተማዋ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ አድርገው ይተነትኑታል፡፡ ይህ ሰም እና ወርቅ ያለው ስትራቴጂ ነው፡፡ ላይ ላዩን ሲያዩት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቃሚ እንጂ አዲስ አበባን የመሰልቀጫ ስልት አይመስልም፡፡ ከተሞች ፍትሃዊ የሥራ ዕድል ክፍፍል እንዲኖራቸው ሲባል ሦስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈፃሚው እና ሕግ ተርጓሚው መቀመጫቸው በተለያዩ ከተሞች እንዲሆን ምክረ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡ እዚህ ላይ የደቡብ አፍሪካ ልምድ እንደ ተሞክሮ ይጠቀሳል፡፡ ሦስት ዋና ከተሞች አሏት፡፡ ኢትዮጵያ ሦስት ወይም አራት ዋና ከተሞች እንዲኖሯት ከኦሮሞ ብሔርተኞች የሚታየው ፍላጎት ግን ከቅን ይቦና የመነጨ እንዳልሆነ የሽመልስ አብዲሳ ንግግር የማያሻማ ማሳያ ነው፡፡ ፍላጎቱ አዲስ አበባን ማዳከም ብሎም ማጥፋት እስከሆነ ድረስ የፌዴራል መንግሥቱን መቀመጫ በመበታተን አይቆምም፡፡ ቀጥሎ በአዲስ አበባ የሚኖረው የፌዴራል መንግሥት ለኦሮሚያ ‹ክልላዊ› መንግሥት ኪራይ እንዲከፍል ይጠይቃሉ፡፡ አልከፍልም ካለ በሃይል የሚያስገድድ ጅምላ ጨፍጫፊ ቡድን አላቸው፡፡ ይህንን በተመለከተ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ከአንድ አመት በፊት ‹‹በአዲስ አበባ ውስጥ የሚደረጉ የልማት ሥራዎችን የማይደግፉ የፌዴራል ተቋማትን የመሬት ይዞታ እነጥቃለሁ›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በተዘዋዋሪ የፌዴራል መንግሥቱ ለከተማ አስተዳድሩ ግብር ይክፈል እንደማለት ነው፡፡ የፌዴራል ተቋማት ድጋፍ ማድረግ ካለባቸው ለአዲስ አበባም፣ ለአሰበ ተፈሪም፣ ለአዲግራትም፣ ለዱርቤቴም፣ ለሐሙሲትም እንጂ ለአዲስ አበባ በተለየ የሚገደዱበት አመክንዮ የለም፡፡ ትኩረቱም አዲስ አበባን መጥቀም አይደለም፡፡ ወደ ዋነኛው ጥያቄያቸው፤ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ተጠቃሚነት ለመሽቀንጠር እንጂ፡፡ ታከለ ኡማ ይህንን ማስፈራሪያቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ለመተግበር ሞክረዋል፡፡ ቤተክርስቱያኗ ለዘመናት ይዛው በቆየችው መሬት ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሰጭ እና ነጣቂ ሆነዋል፡፡ የሀገረ መንግሥት ግንባታን እና አስተዳድርን ያስተማረች ቤተክርስቲያን እንደ ሱቅ በደረቴ የምትቆጠርበት መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ደርሰናል፡፡ ቅዱስ ፓትሪያርኩ አንገታቸውን አቀርቅረው የሚያለቅሱበት ሥርዓት ላይ ነው ያለነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የመቃብር ቦታ በማጣት የሚቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነትም ገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ይጠቀሳል፡፡ አቶ ታከለ ኡማ ከላይ የተጠቀሰው ማሰፈራሪያቸውን አሁንም ቀጥለዋል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ነባር ሰፋፊ የመሬት ይዞታቸውን አስከብረው የሚቀጥሉት ኢምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ያሉትን ለመንጠቅ ነው ዝግጅቱ፡፡ በቅርቡ የመሬት ምዝገባና ኦዲት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡን ማማረር
የኑሮ ውድነትን መጨመር ሌላኛው የአዲስ አበባን ተፈላጊነት መቀነሻ ስልት ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች በተደጋጋሚ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይዘጋሉ፡፡ ሽመልስ አብዲሳ ኦሕዴድ አደራጃቸው፣ ሰልፍ እንዲወጡም፣ ሰልፍ እንዲበትኑ ያዝዛቸዋል የሚላቸው ወጣቶች ናቸው የሚዘጉት፡፡ በመንገዶች መዘጋት የግብርና ውጤቶች ወደ ከተማዋ መግባት አይችሉም፡፡ ከጤፍ እስከ አትክልት አቅርቦት በመቀነሱ ዋጋው እየናረ ነው፡፡ 16 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩትን በ40 ብር እየገዛ ነው አዲስ አበቤ ኑሮን የሚጋፈጠው፡፡ ለዚህ መፍትሔ ሆኖ የቀረበው ‹በከተማ ግብርና ፕሮጀክት አዲስ አበባ ራሷን ትቻል› የሚል ነው፡፡ የትራንስፖርት ችግሩ ከወትሮው ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የኮሮና ተህዋሲ ወረረሽኝ ዱብዳ እንደመሆኑ የሚያስከትለውን ጫና ተጋፍጦ ለዜጎች ድጎማ ማድረግ የመነረበት መንግሥት ነበር፡፡ ነገር ግን ችግሩን ሙሉ በሙሉ ዜጋው እንዲሸከመው ተደርጓል፡፡ በአዲስ አበባ ታክሲዎች ቀድሞ ከነበረው በግማሽ ቀንሰው እንዲያሳፍሩ ሕግ ወጥቷል፡፡ ታሪፉ ደግሞ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ወረረሽኙ ለሁሉም እኩል የተሰጠ በመሆኑ ጭማሪውንም ቢቻል መንግሥት መሸፈን ነበረበት፡፡ ይህ ካልሆነ እንኳን መንግሥት፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች እና ዜጎች እኩል ነው መክፈል ያለባቸው፡፡ ችግሩን ዜጎች ብቻ እንዲሸከሙት መደረጉ ግን ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም በተለየ አዲስ አበባ ላይ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ እነኝህ በነባሪ (by default) የሚፈጠሩና ከተማዋን አቶ ሽመልስ እንዳሉት የማትረባ፣ ለኑሮም ሆነ ለሥራ የማትመረጥ የማድረግ አቅም ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የሽመልስ ንግግር በግለሰብ ደረጃ የሚታይ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚንስተር አብይን ጨምሮ የኦሕዴድ ሰዎች ተስማምተው ያፀደቁት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ አስቀድሞ በኦነግና ኦሕዴድ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ በጋራ ሊሠሯቸው ካሰቡት ውስጥ አንዱ አቶ ሽመልስ የተናገሩት እና አቶ ታከለ እግር በእግር አዲስ አበባ ላይ ገቢራዊ እያደረጉት ያለው ከተማዋን የማጥፋት ሥራ ነው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ስለ አዲስ አበባ የተናገሩት 5ቱ የኦሮሞ ድርጅቶች በጋራ መግለጫቸው ካነሱት ተመሳሳይ ነው፡፡ ሃሳባቸው ተቀርፆ ስላልሰማነው እንጂ ሌሎች የኦሕዴድ አመራሮች ከአቶ ሽመልስም የከፋ ፀረ ኢትዮጵያ ኃሳብ እንዳላቸው ንግግራቸው ያሳብቃል፡፡ ‹‹. . . ፈቃዱ እንዳለው በሃይል መደረግ የለበትም፡፡›› ይላሉ፡፡ በድምሩ የከተማ ግብርና፣ የልማት ተነሽ አርሶ አደር ልጆች በታላላቅ ፕሮጀክት ደረጃ አዲስ አበባን ለማጥፋት እየተሠራባቸው ያሉ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራውና ‹ሸገርን ማስዋብ› የተባለው ፕሮጀክትም ከእነዚህ ጋር የሚዳበል ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን መቀመጫ ማሳጣትና ነዋሪውን ማማረርም ከተማዋን ለማዳከም የተቀረፁ ይመስሉኛል።
(ፍ -ት-ሕ መፅሔት ሁለተኛ ዓመት ቁጥር ነሐሴ 2012 ዓ.ም.)