በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጥቃት በጥብቅ እናወግዛለን

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይርተሰጠ መግለጫ
በጥር 22/2017 ዓ.ም በአውሲ ራሱ ዞን ኤሊዳር ወረዳ ኪያሩ ቀበሌ በደረሰ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት የሚሆኑ የአፋር ወገኖቻችን መሞታቸው ታውቋል። ጥቃቱ የተፈፀመው በጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ድሮን መሆኑን የጅቡቲ መንግስት ያመነ ሲሆን፣ ነገር ግን በራሱ ግዛት ላይ እንደተፈፀመ አሳውቋል። እንደ ምክንያት የጠቀሰውም የሽብር ጥቃትን ለመከላከል እንደሆነ ገልጿል። የአፋር ክልል ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ጭምር ግን ጥቃቱ በአፋር ክልል ላይ እንደተደረገ እና በጥቃቱም ንፁሀን እንደተገደሉ እማኝነታቸውን ገልፀዋል።
ሆኖም የኦህዴድ-ብልፅግና አገዛዝ ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም። ይህም አገዛዙ በህዝብ ላይ ለሚደርስ ሞት እና ውዥንብር ደንታ ቢስ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይህ በርሀብ፣ በኑሮ ውድነት፣ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት… ወ.ዘ.ተ ፍዳውን እየበላ የሚገኝ ህዝብ ላይ ተጨማሪ የድሮን ድብደባ ሲደርስበት እጅግ አሳዛኝ ነው። ከደረሰው ግድያ ባልተናነሰ በተለይ አደጋው በሚመለከታቸው ተቋማት ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱ አሳዛኝነቱን ያጎላዋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ሞት እና ጉዳት እያዘነ ፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል። አገዛዙም በአስቸኳይ በንፁሀን ላይ ለደረሰው ግድያ እውቅና እንዲሰጥ እና በአስቸኳይ ግልፅ ማብራሪያ እንዲያቀርብ ፓርቲው ያሳስባል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
