በንፁሐን ሞት እና ሰቆቃ የሚተከል አሻራ፣ የሚፀና ወንበር የለም
በንፁሐን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሠጠ መግለጫ
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሶስት አሰርት ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፀሐይ በታች በሰው ልጆች ላይ ያልተፈፀመ ግፍ የለም፡፡ የአማራ ሕዝብ በስርዓት እና በመዋቅር በተደገፈ ሁኔታ የእልቂት ሰለባ መሆኑ የአደባባይ እውነት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ይሁን እንጂ ሰውን እንደ ሰው በማይመልከት የነገድ ስርዓት ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከገዳዮች ሰይፍ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ይህን አውነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ፣ትናንት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸው የተቀጠፈበትን እና በርካቶች አካላቸውን ያጡበትን የሰሜን ኢትዮጵያን እልቂት ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል፡፡
በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ አምባ ገነን መሪዎች ባሕሪያቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ለራሳቸው ስልጣንና እርካሽ ዝና ሲሉ አንድን ሕዝብ ወይንም ማሕበረሰብን ለአረመኔ ፖለቲካቸው እዳ ከፋይ እንዲሆን ይፈርዱበታል፡፡ ይህ የነገድ ፖለቲካ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ምድር ዛሬም ከትናንቱ የባሰ ዋጋ እያሰከፈለ ነው፡፡ ሁሉም አካል ሊገነዘበው የሚገባ እውነት ቢኖር አንዱን ገድሎ አንዱ ሊኖር አይችልም፡፡እመራዋለሁ የሚለውን ሕዝብ የሚወጋ አገዛዝም ሆነ ነፃ አውጭ ቡድን ንፁሐንን በመግደል የሚተክለውም አሻራ፣ የሚያፀናውም ወንበር አይኖርም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የበርካቶች ዝምታ፣ለገዳዮች መተባበር መምሰሉ ሀዘኑን እና ጥፋቱን መሪር አድርጎታል፡፡ ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እኩያን ሀይሎች በንፁሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ግፍ እያጋለጠ እና ግፈኞችን በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ይገኛል፡፡
‘’በአማራ ክልል’’ በብልፅግና አገዛዝ ከሰማይ በድሮን ከመሬት በታንክ፣በመድፍ፣በዙ23 እና በዘመናዊ መሳሪያ በርካታ ሰዎች በእየ ቀኑ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ አርጌ (ዝብስት) ከተማ ላይ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም የብልፅግና አገዛዝ ከ40 በላይ ንፁሐን ሰዎችን በድሮን ጨፍጭፏል። የድሮን ጥቃቱ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ በመፈፀሙ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ሕፃናት እና አረጋዊያን ተጨፍጭፈዋል፡፡ በድሮን ጥቃት ከሞቱት ንፁሀን በተጨማሪ በርካቶች መቁሰላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጠናል። በተመሳሳይ ቀጠና በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ አዲስ ቅዳም ከተማ ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም የአገዛዙ ሠራዊት ቤት ለቤት በመዞር እና መንገድ ላይ ያገኙትን ከ20 በላይ ንፁሀኖች ገድለዋል፡፡ ከተገደሉት ንፁሐኖች አብዛኞቹ ሕፃናት እና ወጣቶች መሆናቸውን የተጎጅ ቤተሰቦች ለዜና አውታሮች ገልጸዋል።
የአማራን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀው ጠባብ ብሔርተኝነት የተጠናወተው አገዛዝ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ የለን ቀበሌ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም የብልፅግና አገዛዝ በፈፀመው የድሮን ጥቃት አምስት ንፁሀን ተገድለዋል፡፡ በጥቃቱ ከተገደሉት ንፁሀን መካከል የሰባ ዓመት አዛውንት ይገኙበታል። ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ቦራ ወረዳ ቢጢስ ቀበሌ በሰው ደም በሰከሩ ታጣቂዎች ከሰላሳ በላይ ንፁሐን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ በዚህ አረመኔ ቡድን ከተጨፈጨፉት ንፁሀን መካከል ሕፃናት፣አረጋውያን እና እናቶች ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ በሁለት ቦታዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ካራ ከተማ አካባቢ እና ባጮ ፋሉሚ በተባሉ ቦታዎች በርካታ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ተገድለዋል፡፡ በዚህ ጥቃት ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ፓርቲያችን የደረሰው መረጃ አረጋግጧል፡፡
በዚሁ ጥቅምት ወር ከሳምንት በፊት ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ አድዓ መልኬ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የገንዳ አረቡ መስጅድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ መኪን ሀጂ አረፉን ጨምሮ አስራ ሁለት ሰዎች በሽብርተኛ ሀይሎች ተገድለዋል። ኢማሙ እና የኢማሙ አስራ አንድ የቅርብ ቤተሰቦች ከመገደላቸው በተጨማሪ በርካቶች ታግተው መወሰዳቸውን የተጎጅ ቤተሰቦች አብራርተዋል፡፡ይህን አረመኔ ተግባር የፈፀመው ሽብርተኛው የኦነግ ሸኔ ቡድን የገደላቸውን ንፁሐኖች ለመልቀቅ በሚል ሶስት ሚሊዩን ብር ጠይቆ 1.4 ሚሊዮን ብር ተለምኖ ተሰጥቶታል፡፡ ንፁሐን ሰዎችን መግደል ፣ማገትእና መዝረፍ የሽብርተኛው ኦነግ ሸኔ ቡድን የተፈቀደ ደንበኛ ስራ በሚመስል መልኩ ቀጥሏል፡፡ የእርስ በእርስ ግድያ ፣ማፈናቀል እና ዘረፋ የስርዓቱ መርሆዎች ተደርገው የሚተገበሩ ይመስላል፡፡
“ሀዘንሽ ቅጥ ያጣ፣ ከቤትሽ ያልወጣ፤
የሞተው ወንድምሽ ፣የገደለው ባልሽ፤
አሁን እንዴት ብሎ፣ ይወጣል ሀዘንሽ፤’’
ኢትዮጵያን ዘርፈው ሲከብሩ ዞረው መውጋት እና እርስ በእርስ ማጋደልን የእውቀት ጥግ አድርገው የሚቆጥሩ ጎሰኞች የሚፈፅሙትን አረመኔነት ከላይ የሰፈረው ስንኝ በሚገባ ይገልፀዋል የሚል እምነት አለን፡፡
ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት እና ሰቆቃ እንዲቆም በርካታ ጊዜ በመግለጫ አሳስቧል፡፡ ዛሬም ፓርቲያችን በቅርቡ ከሚተገብራቸው የሰላማዊ ትግሎች አስቀድሞ የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፡፡
- የዜጎቹን ሕይዎት መታደግ ያልቻለው የብልፅግና አገዛዝ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንዲሆን፣
- ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከአርምሞ እና ውዥንብር ወጥቶ ይሕን ግፍ በአደባባይ እንዲቃወም፣
- የእምነት፣ የሲቪል ተቋማት እና ልዩ ልዩ ማሕበራት ተጎጅዎች ፍትህ እንዲያገኙ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፣
- ከሀገር ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እርስ በእርስ ከመከፋፈል ወጥቶ አንድነቱን በማጠናከር በሀገር ቤት እየተካሄደ የሚገኘውን ሰላማዊ ትግል በማጠናከር የስርዓቱን ኢ ሰብአዊ ድርጊት የማጋለጥ ስራውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻ በሞቱ ወገኖቻችን የተሰማንን መሪር ሀዘን እየገለፀን በዝምታ ገዳዮችን ከመተባበር ወጥተን ለሀገራችን አንድነት ሁላችን ለሰላማዊ ትግል መነሳሳት እንዳለብን በአንክሮ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
የባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ህዳር 03/ 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ