ስር የሰደደው የዐቢይ የተቋም አተካከልና ክትትል ችግር (ገለታው ዘለቀ)
ከሁለት አመታት በፊት በሃገራችን የፖለቲካ ለውጥ የሸተተን መስሎን ስለ ሽግግር ብዙ አልን፤ እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ለውጡ መጣሁ መጣሁ ሲል በፍጥነት የሽግግር መንግሥት ማቋቋም አለብን የሚል ድምጽ አሰሙ:: ይህ ድምጽ ግን በጣም የጥቂቶች ነበር:: አብላጫው ሰው ዶ/ር አብይ የሚመሩት መንግሥት የሽግግሩን ሥራ ይስራው የሚል ነበር:: ለለውጡ በጣም የሳሱ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የዶ/ር አብይን መንግሥት በርታ፣ ጎበዝ፣ እሰየው—– ካልነው እየገፋ ይሄዳል የሚል ሳይንስ የጎደለው ዝንባሌ አሳይተዋል:: ያለ ሽግግር መንግሥት ኢትዮጵያ ወደ ተፈላጊ ለውጥ ልታልፍ አትችልም:: ስለዚህ በአስቸኳይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው ቀጭን ድምጽ ከዚህም ከዚያም ዱላ በዛበት:: የሽግግር መንግሥት አያስፈልግም በዚህ የለውጥ ኃይል ላይ ሌሎች ለሽግግሩ የሚያግዙ ተቋማት ከተገነቡ እነዚህን ተቋማት ይዞና ክፍተቱን ሞልቶ የለውጡ ኃይል ራሱ ሽግግሩን ይመራዋል ተባለ:: ብዙ ሰው ለለውጥ ስለጓጓና የህወሃት ዘወር ማለት ስላስደሰተው ጠንከር ብሎ ሳይመራመርና ሳይጠይቅ ለዶ/ር አብይ ዲስኩሮች ጭብጨባውን አቀለጠው:: እኚህ ሰው ወደ ስልጣን ሲመጡ የለውጥ ኃይል በራሱ ሽግግር ለመምራት ምሉዕ የመሆን ተፈጥሮ ስለማይኖረው ለሽግግሩ አጋዥ የሆኑ ተቋማትን መፍጠሩ ነገር በጉጉት ተጠበቀ::
ታዲያ ሲጠበቁ የቆዩት ጠቅላይ ሚ/ር ከሚጠበቁት ተቋማት መካከል የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽንና የማንነት፣ የአስተዳደርና ወሰን ጉዳይ ኮሚሽንን አቋቋሙ:: “ጠቅላይ ሚኒስትሩ” እነዚህን ተቋማት ሲተክሉ የነበሩትን ችግሮች በመዘርዘር የእኚህን ሰው የሲስተምና የተቋም አገነባብ ችግር እስቲ ዛሬ እንወያይበት፡
1.ሲስተምና ሚኒስትሪ የዶ/ር
አብይን የተቋም አተካከል መሠረታዊ ችግር ያየሁትና የፍልስፍና ችግሮቻቸውን የተማርኩት የሰላም ሚንስቴር የሚባል የሚንስቴር መስሪያ ቤት ሲመሰርቱ ነው:: ይህ ተቋም ሲመሰረት የመጀመሪያው ጉዳይ “ሰላም” የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ የተረዱበት መንገድ ነው የገረመኝ:: ሰላም እውነት ነው ለአንድ ማህበር / ሃገራዊ ሕብረት / እጅግ ወሳኝ የሆነ መተሳሰሪያ መርሆ ነው:: ሰላም ብቻ አይደለም ነገር ግን ፍቅር፣ በጎነት፣ መተሳሰብ፣ የመሳሰሉት ረቂቅ በጎ ነገሮች ሁሉ ለሕብረተሰባችን እጅግ አስፈላጊ መተሳሰሰሪያ መርሆዎች ናቸው:: ሀብታም ሆነን ነገር ግን ሰላም ባይኖረን ሃብታችን ምን ይፈይዳል? ምን ዋጋ አለው? ሁሉ ኖረን ፍቅር ግን ቢጎድለንና በብሔሮች መካከል ወይም በዜጎች መካከል መተማመን ቢጠፋ ፍቅራችን ቢተንብን ሃብታችን ከቶ ምን ይጠቅመናል? እውነት ነው ሰላም ፣ ፍቅር፣ በጎነት፣መተማመን፣መረዳዳት እና ሌሎች አስፈላጊ መርሆዎች ሁሉ የህብረታችን እጅግ አስፈላጊ የመተሳሰሪያ መርሆዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህ መተሳሰሪያ መርሆዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የምናቋቁምላቸው አይደሉም። የፍቅር ሚንስቴር፣ የበጎነት ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚንስቴር፣ ወዘተ እያልን መንግሥታዊ ተቋም አንመሰርትላቸውም። ለምን ቢባል እነዚህ ‹ኤለመንቶች› በተፈጥሮ አንድ ገዢ ፓርቲ የሚመራቸውና የአንድ አካል ውጤት አይደሉም። የብዙ ተቋማት፣ የሃይማኖትና የባህል ውጤቶች ናቸው እንጂ በተፈጥሯቸው የመንግሥት ተቋማት አይደሉም:: ነፃ ተቋማት ናቸው:: መንግሥት ሰላምን ፖለቲካዊ ሊያደርገው አይችልም:: ሰላም በተፈጥሮው ገለልተኛነትን፣ ነፃነትን ይጠይቃል:: መንግሥት ከአንድ ሃገራዊ ኃይል ጋር ቢጋጭ የሰላም ሚኒስቴር ጣልቃ ገብቶ የመካከለኛነት ሚና ሊጫወት አይችልም:: የዶ/ር አብይ ፍልስፍና ችግር ይህ ነው:: ሰላምን ፖለቲካዊ በማድረጋቸው ሠላምን ጎድተዋል፤ ተቋሙን ጎድተዋል:: በሀገራችን ሊመሠረቱ የሚችሉ የሰላም ገለልተኛ ተቋማት እንዳይፈጠሩ አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል::
ሁለተኛው የዚህ የሰላም ሚኒስቴር ተቋም ችግር ይዘቱ ነው:: በሰላም ሚኒስቴር ስር ያሉት ተቋማት ከዚያም ከዚህም የተሰበሰቡ ተቋማት ናቸው:: እነዚህን ሁሉ በአንድ ቋት ውስጥ አስገብቶ የሰላም ሚኒስቴር ማለት እውቀት የጎደለው ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ የሚጋጩ ሁኔታዋችን ያመጣል:: ስለ ሰላም ስናስብ ትምህርት፣ ፖሊስ፣ ወታደር ሁሉም በአንድም በሌላም መንገድ ለሰላም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይታሰባል:: ነገር ግን እኚህ ሰው ከተቋማቱ የተወሰነውን መርጠው ለሰላም የቀረበ ሌላውን ራቅ ያለ አድርገው ማሰባቸው ሌላው የአምክኖት የተቋም አተካከል ችግራቸውን ያሳያል:: ሰላም በገለልተኛ ተቋማት፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በትምህርት ተቋማት ቢያዝ ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት ሽምግልናን ለማምጣት ያስችላል። ለምሳሌ መንግሥት ከአንድ ኃይል ጋር ቢጣላ የሰላም ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈርያት ሽማግሌ ሆነው መቅረብ አይችሉም፤ ለሰላም መካከለኛ ስር የሰደደው የዐቢይ የተቋም አተካከልና ክትትል ችግር ገለታው ዘለቀ (የባልደራስ ፅህፈት ቤትና ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ) ፖሊሲ 10 አይሆኑም። ዶክተር አብይ ሰላምን የተረዱበት መንገድ ስህተት ነው።
ለሰላም ሚንስቴር ተጠሪ ከሆኑት ተቋማት አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት ለደህንነት መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የነበሩ መሆናችው ይታወቃል:: ለአብነትም ፌዴራል ፖሊስ፣ ይጠቀሳል::
የሰላም ሚንስቴር ወደ ‹ክልሎች› እና ከተማ አስተዳደሮች በሚወርድበት ጊዜም በቀጥታ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ጋር የተዳበለ ነው:: በ‹ክልል›ና ከተማ አስተዳደር ደረጃ ‹የሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ›፣ በዞን/ክፍለ ከተማና ወረዳ አደረጃጀት ደግሞ በዚሁ ስያሜ መምሪያና ፅህፈት ቤት ተብሎ በቅደም ተከተል ይወርዳል:: ዛሬ አዲስ አበባ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አቻ ተቋማት የሚሰጧቸውን ጋዜጣዊ መግለጫዎች የሚፈቅደውና የሚከለክለው የሰላም ሚንስቴር ሆኗል:: ነገሮች ለመንግሥት ሥልጣን አስጊ መሆን አለመሆናቸውን የሚሰልለው ሀይል በዚሁ በሰላም ሚኒስቴር በኩል ነው:: በመሆኑም ሰላም ሚንስቴር ከላይ ሲታይ የአሸማጋይነት ሚና ያለው የሚመስል ስም ተሸክሞ ውስጡ ግን የስለላ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል::
2.የአዲስ አበባ የሰላም ም/ቤት
ይህ ተቋም ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የጠቅላይ ሚንስትሩን ፈለግ ተከትለው ከታከለ ኡማ የምክትል ከንቲባነት ሥልጣኑን እንደተቀበሉ ያቋቋሙት ነው:: ሥራው በቀጥታ ፀጥታን ከማስከበር ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ገልፀዋል:: አዲስ አበባ የራሷ መደበኛ ፖሊስ አላት፣ ‹ተወርዋሪ ኃይል› የሚባል ልዩ የፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም ከላይ በተጠቀሰው ተዋረድ መሠረት የሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ አላት:: አዲሷ ከንቲባ የፈጠሩት ተቋም ተመሳሳይ ሥራ የሚሠራ ሌላ ተቋም ነው:: ሰላምን ፖለቲካ የማድረጉን ሥራ በቀጥታ የወሰዱት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ነው::
- የማንነትና አስተዳደር ወሰን ኮሚሽን
ሁለተኛው የዶ/ር አብይ የተቋም አተካከል ችግር የሚታየው ደግሞ በማንነት አስተዳደርና ወሰን ኮሚሽን ላይ ነው:: ይህ ተቋም ሲተከል ወደ ግማሸ መቶ ሰዎችን የያዘ ሲሆን የተለያዩ የፖለቲካ መሪዎችን ከዚያም ከዚህም አጠራቅመው የተከሉት ተቋም ነው:: ከማንነት ጋር፣ ከአስተዳደር ወሰን ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ገለልተኛ ሆኖ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ነው ተብሎ ነበር የታሰበው:: ይህ ኮሚሽን ሲቋቋም እኔ እራሴ ደስ ብሎኝ ነበር:: ይሁን እንጂ በጽሞና ሳየው ይህንን ኮሚሽን ያቋቋሙት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚያም ከዚህም ተሰባስበው በመሆኑ የውቅር ችግር እንዳለው ያሳያል።
ይህ ኮሚሽን ከአተካከሉ ችግር እንዳለበት ማሳያ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል በኮሚሽኑ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸውን ሁሉ ማካተቱ ነው:: ይህ ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም:: በአጠቃላይ የማንነት፣ አስተዳደርና ወሰን ኮሚሽን ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ፣ ሽግግሩን መስመር ለማስያዝ አጋዥ ኮሚሽን ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን የጠ/ሚኒስትሩ ተቋም አመሠራረት ችግር ይሄውና ይህንን ኮሚሽን አንካሳ አድርጎታል:: ለሽግግሩ ደራሽ አልሆነም:: ባለበት ሳይንቀሳቀስ የሥራ ዘመኑም ሊጠቃለል ነው:: በአሁኑ ሰዓት እኚህ ሰው ከዚያም ከዚህም የማይግባቡ ፖለቲከኞችን ሰብስበው አጠራቅመው የመሰረቱት ኮሚሽን በአሁኑ ሰዓት ብዙዎቹ ከኮሚሽኑ ጋር ግንኙነትም የላቸውም:: ይህንን አስፈላጊ ኮሚሽን ዶ/ር አብይ ሲተክሉ ስላበላሹት ለሽግግሩ ደራሽ አልሆነም:: እኚህ ሰው በአንድ በኩል ይህንን ኮሚሽን አቋቋሙና ደቡብ የማንነት ጥያቄ ተነሳ ሲባል በአባ ዱላ የሚመሩት የማንነት ኮሚቴ መሠረቱ እየተባለ ሲወራ ነበር:: እውነት ሆነ ውሸት ሰውየው ግን የተቋም አተካከልና ክትትል መሠረታዊ ችግር እንዳለባቸው በጣም ተምረናል:: ይህ ኮሚሽን ነጻ ሆኖ መፈጠር ነበረበት።
- የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን
ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ ስትገባ ሽግግሩ የተሻለ እንዲሆን ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ተቋማት መካከል የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን ነበር:: ይህ ኮሚሽን እንዲቋቋም ብዙ ግፊት ነበር:: ዶ/ር አብይ ይህንን ኮሚሽን በፍጥነት አቋቁመው ሽግግሩን እንዲያሳልጡ ሲመከሩ ቆይተዋል:: የኮሚሽኑ አስፈላጊነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉ ክፉ ትውስታዎችን ለማጽዳት፣ በካሳ ላይ ያተኮረ ፍትህ በማምጣት ብሔራዊ ፈውስ ማውረድ፣ በመካከለኛነት አገልግሎት ለጠፉ ጥፋቶች ፍትህን ማውረድ፣ የተጣላን ማስታረቅ ነበር:: ይሁን እንጂ እኚህ ሰው ይህንን ኮሚሽን ሲያቋቋሙ ወዳጃቸውን የኢዜማ መሪ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምረው ሌሎች የፖለቲካ መሪዎችን ሳይቀር ከሃይማኖት መሪዎቹ ጋር አቀላቅለው ፈጥረውታል:: ብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን በገለልተኛነት የሚመራ ተቋም ነው:: የሽምግልና ቁጥር አንድ መርህ ገለልተኛነት ነው ይባላል:: እኚህ ሰው አወላክፈው የፈጠሩት ብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን ሽግግሩን እያገዘ አይደለም:: አልፎ አልፎ የተወሰኑ ሰዎች በቴሌቭዥን ብቅ እያሉ አለን ቢሉም ኮሚሽኑ የለም:: የማንነት አስተዳደርና ወሰን ኮሚሽንም ሆነ የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን ሽግግሩን ለማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር:: ይሁን እንጂ ዶ/ር አብይ አወላክፈው ስላቋቋሙት እነሆ ቢሮው ክፍቱን እንዲሁ ይውላል::
- የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ
ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ብዙ ሰው ደግፎ ነበር። አብዛኛው ድጋፍ በህወሃት ጥላቻ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ግን ትክክል አልነበረም። የትግላችን ግብ ህወሃትን ገለል ማድረግ ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ነበር። የሆነ ሆኖ ዶክተር አብይ ከሃገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ለመሰብሰብ ሞክረው ነበር። ያቺን ጊዚያዊ ተቀባይነት አይተው ይሆናል ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው ገንዘብ እንዲያዋጡ አንድ ሃሳብ አመጡ። ይህ ሃሳብ በራሱ መልካም ነበርና ሁላችንም ደግፈናል። ውጭ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ተደራጅተው ቢረዱ በጣም ተገቢ ነው። እንዴውም እስካሁን ብዙ በዚህ ጉዳይ ላይ አልሠራንምና ብዙ ልንሠራ ይገባል። የዶክተር አብይ ችግር ይህንን ሃሳብ ወደ ተቋም ሲቀይሩ ነው። እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ኢትዮጵያውያን ሃገራችሁን ደግፉ የሚል ምክርና ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ራሳቸው ቦርድ ሾመው አደራጅ መሆናቸው ግን ከባድ ስህተት ነበር። ይህ ተቋም በተፈጥሮው ነጻ ነው መሆን የነበረበት። ይህ ተቋም በዶክተር አብይ ሹመት የሚመራ ከሆነና ፖለቲካዊ ከሆነ የህዝቡ ድጋፍ ከፖለቲካው ሙቀት ጋር ይዋዥቃል። ለዚህም ነው የዶክተር አብይ ቅቡልነት መውረድ ሲጀምር አንዳንዶች ያዋጡትን ገንዘብ መልሱልኝ እስከማለት የደረሱት። ይህ ተቋም ከፖለቲካ ሹመት ጋር ባይገናኝ ኖሮና ነጻ ቢሆን ሁሉን አቃፊ ስለሚሆን ተቋሙ ያድግ ነበር። የዶክተር አብይ የተቋም አመሠራረት ችግር አንዱ ማሳያ ይህ ነው። ዛሬ ይህ ተቋም ከፍተኛ የቅቡልነትና የማንነት ኪሳራ ውስጥ ገብቷል። ትረስት ፈንድ በአንድ በኩል አሜሪካ ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ ቢሆንም ነገር ግን የዶክተር አብይ ተቋም ሆኖ ያገለግላል። ሲቪክ ድርጅቶች ነጻ መሆን አለባቸው።
- የዶክተር አብይ ርዕይ
ስለተቋም ስናነሳ ተቋም የርዕይ ማስፈጸሚያ አንድ ብርቱ መሳሪያ ነው። የዶክተር አብይ ርዕይ አረንጓዴ አሻራ ነው ይላሉ። መቼስ ልዩ ልዩ ተክሎችን መትከል መናፈሻ መሥራት አስፈላጊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ለዚህ ጠቅላይ ሚንስትር መሆን አያስፈልግም። ከከንቲባዎች በታች ባለሙያዎች ይህንን ይሠሩታል ያስተባብራሉ። አሁን ኢትዮጵያ የምትሻው ጠቅላይ ሚንስትር ከፍተኛ የሆኑ መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣት፣ ብሄራዊ መግባባትን ማምጣት፣ ሃገሪቱን ለምርጫ ማዘጋጀት፣ መተሳሰሪያ መርሆዎቻችን እንዲሻሻሉ መሥራት፣ የመንግሥት ቅርጻችንን ለማሻሻል መሥራት የመሳሰሉትን ጉዳዮች ለመሥራት ነው። ዶክተር አብይ ይህንን ነበር ማለም የነበረባቸው። ነገር ግን የሳቸው ህልም የተለያዩ መናፈሻዎች ሆነው ቀርተዋል። ለውጥ ያስፈልገናል።