መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው የዘር ማጥፋት ወንጀልን በጽኑ እናወግዛለን !
ባለፉት ዓመታት በተለይ “ለውጥ” መጣ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል በአይነቱ እና በመጠኑ እየጨመረ መጥቷል ። ለዚህም ዋንኛው ምክንያት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት እንደሆነ ብዙ አስረጂ የሚሻ ጉዳይ አይደለም ።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ የተፈጸመው የዘር ፍጅት ወንጀል ከዚህ ቀደም በክልሉ ሲፈጸም ከነበረው አረመኔያዊ ተግባር የተለያየ አይደለም ። በዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ወዳጅች እና ዘመዶች ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጥልቅ ሐዘን ይሰማዋል።
ባለፉት ዓመታት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል ለማስቆም “መንግስት ነኝ” የሚለው አካል አንዳች ተጨባጭ ነገር ሲያደርግ አልታየም ። ለዚህ ሁሉ ዕኩይ ተግባር “መንግስት” ተጠያቂ እያደረገ ያለው ኦነግ ሸኔ የተባለውን ገዳይ ቡድን ነው። ሆኖም ግን ይህ የዳቦ ስም የተሰጠው ገዳይ ቡድን “መንግስት ነኝ” ከሚለው ኃይል በትጥቅ ሆነ በስንቅ በልጦ አይደለም ። ከምንም በላይ ደግሞ “መንግስት” ንፁሃንን መታደግ ዋንኛ ተግባር መሆን ነበረበት። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ አይደለም በተደጋጋሚ እንዲህ አይነቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ፍጅት ወንጀል በአይነቱ እና በመጠኑ እየጨመረ ለመምጣቱ ዋናው ምክንያት መንግስታዊ ሽፋን ያለው ወንጀል እንደሆነ ባልደራስ አጥብቆ ያምናል።
ይህም በመሆኑ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው ለደረሰባቸው እና ለሚደርስባቸው የዘር ፍጅት ወንጀል፣ እንዲሁም ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ዳተኝነት በማሳየት ብቻ ሳይሆን ለዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚ ቡድን ሽፋን በመስጠት ጭምር አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው። “መንግስት” ዋንኛ ተጠያቂ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ሥር- ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከሚያከናውናቸው የፖለቲካ ትግል ባሻገር ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመሆን ይህንን ጉዳይ ከአገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ የሕግ ተቋማት በመውሰድ ወንጀለኞች በፍትሕ አደባባይ እንዲዳኙ በማድረግ የንጽሃን ደም ደም ከልብ ሆኖ እንዳይቀር አጥብቆ ይሰራል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ