መንግሥታዊው የገዳ ወረራ (ስንታየሁ ቸኮል፤ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት (የህሊና እስረኛ))
(በተለይ ለኢትዮ 360 ሚዲያ የተላከ)
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. የአክቲቪስት አጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተሰማ በኋላ በሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ተከስተዋለል፡፡ አምባገነኑ የአብይ አሕመድ ቡድን ክስተቱን ተገዳዳሪዎቹን ሁሉ የመደብደቢያ ዱላ አድርጎታል፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ፖለቲካዊ አሰላለፎች እንዳልነበር ሆነዋል፡፡ ዜጎች ማሕበራዊ ረፍት አጥተዋል፡፡ ዐማራዎች በየቦታው እየታደኑ እንደ አውሬ መታረዳቸው እጅግ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ መንግሥት ተብየውም አራጅ፤ አሳራጅ ሆኗል፡፡ ፖለቲካዊ ውጥንቅጡ በዐማራ ደም እየዋኘ ወደ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እየቀዘፈ ነው፡፡ መሄጃ ያጣ የስቃይ ድምፅ ከጉራ ፈረዳ እስከ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ከመተከል እስከ ማይካድራ ይጮሃል፡፡ የሚሰማው ግን የለም፡፡ አብረን እንዳንጮህ እንኳን መጮህም ተነፍገን በእስር ቤት እንገኛለን፡፡ ለዚህም ነው በአምባገነኖች የሀሰት ክስ ሀቀኛ ታጋዮች ከታሠርንበት ቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ታጉሬ ይህንን ትንሽ መጣጥፍ የምሞነጫጭረው፡፡ ብቻ ዐማራነት የሞት ቅጣት የሚያስከትል ያልተፃፈ ወንጀል ሆኗል፡፡ ደሙ እንደ አባይ ወንዝ ሀገር አቋራጭ ማዕበል ሆኗል፡፡ ከኢትዮጵያም አልፎ እንደ አባይ ግብፅ፤ ካይሮ ድረስ ይፈሳል፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቃላማ ይዘው የተገኙ ዐማራዎች በዚያው በሚገኙ የኦነግ የመገንጠል አርማ አውለብላቢዎች ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ይህ ሕዝብ ድሮም ኢትዮጵያን ያቆማት ደሙን አፍስሶ እንደነበር ስናስታውስ ታሪክ ያፅናናል፡፡ የኢትዮጵያ የድል ችቦ የሚያበራበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነም አምናለሁ፡፡ በዐማራ ላይ እየደረሰ ያለው የጅምላ ጭፍጨፋ አዋጅ የኦሕዴድ/ብልፅግና የትግል አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ የአዋጁ ደራሲ ጃዋር መሐመድ ብሎም አስፈፃሚዎቹ ሽመልስ አብዲሳ፣ ታከለ ኡማ እና አዳነች አቤቤም የኦሕዴድ/ብልፅግና ቼጉቬራዎች ናቸው፡፡ ታላቁ የጥቃት ማዕከላቸው ደግሞ አዲስ አበባ ነው፡፡
አዲስ አበባን እንደ ወልቃይት
የወያኔ የጥቃት እና የጥቅል ጥቅም (ልዩ ጥቅም ገላጭ አልመሰለኝም) ማዕከላት ወልቃይት፣ ጠለምት እና ራያ ነበሩ፡፡ መተከል፣ ደራ እና አዲስ አበባም የውክልና ማጥቂያ ማዕከላቱ ነበሩ፡፡ ተረኛው ኦሕዴድ/ብልፅግና ደግሞ አዲስ አበባን የጥቅል ጥቅም ማዕከሉ፣ ቤንሻንጉል/ጉምዝን ደግሞ የውክልና ማጥቂያ ማዕከሉ አድርጎ ቀጥሏል፡፡ በሀገራችን ጫፍና ጫፍ የሚሰሙ የጭፍጨፋ መርዶዎችን ወደ መሀል ሀገር ለመሳብ እየሠራ ነው፡፡ አዲስ አበባን እንደ ትንሽ ጉብታ ንዶ ለማፍረስ ተነስቷል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው በወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ሕገ መንግሥታዊ ቅሪት ነው፡፡ አዲስ አበባን የቀውስ ሜዳ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ ባልደራስን ጨምሮ የሕጋዊ ድርጅቶችን ስም በመጥቀስ ፎቶ ግራፍ አሸክሞ በሰላማዊ ሰልፍ ጠባ ጫሪ መፈክሮችን አሰምቷል፡፡ በተደጋጋሚ ከድንጋይ እስከ ቦምብ የታጠቁ መንጋዎቹን በአዲስ አበባ ላይ አዝምቷል፡፡ በጥባጭ ሰራዊት የሚመለምለውም መሬትና ገንዘብ በሕገ ወጥ ሂደት በማደል ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ባለፉት ሦስት ዓመታት ሠርቷል፡፡ በታከለ ኡማ የተጀመረው የሃብት ሽግግር በአዳነች አቤቤ ቀጥሏል፡፡ መንግሥታዊ የመሬት ወረራ እና ንጥቂያው ተፋፍሞ አዲስ አበባን ለማጥፋት እየተሠራበት እንደሆነ የራሱ የመንግሥት ሪፖርቶች ብቻ በቂ ናቸው፡፡ ይህም ለዘመናት ተቋርጦ የነበረው የገዳ ወረራ ዳግም የተጀመረበት ምዕራፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የዚህ ወረራ ማጠንጠኛዋ ደግሞ አዲስ አበባ ሆናለች፡፡ ለዚህም ነው ከተማዋ ራስ ገዝ (አድያም) መሆን አለባት የምንለው፡፡
ገዥው ኦሕዴድም ሆነ እንደ አሸን የፈሉት ተቃዋሚ የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅቶች በአዲስ አበባ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡ ለዘመናት የተቃቡትን ደም ረስተው የሚተሸሹት ስለ አዲስ አበባ ሲያስቡ ነው፡፡ ሁሉም ከተማዋን ለመዋጥ ይጎመጃሉ፡፡ ለዚህም አምስቱ የኦሮሞ ድርጅቶች በኢሊሌ ሆቴል በበቀለ ገርባ አንደበት ያነበቡትን መግለጫ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ ይህንን ከተማ አፍራሽ የፖለቲካ አሰላለፍ ገዥው ፓርቲም ሲቀላቀል በታከለ ኡማ ‹አዲስ አበባ የኦሮሞ የትግል ማዕከል ነች› የሚል መፈክር ታጅቦ ነው፡፡ በቀድሞዎቹ የመዲናዋ ግዛቶች ማለትም በቡራዩ፣ በለገጣፎ እና በሱልልታ ብሎም በገላን፣ በቱሉ ዲምቱ በኮዬፈጨ እና በሌሎችም የአዲስ አበባ አካባቢዎች የተፈፀሙ አረመኔያዊ ድርጊቶች ለውጥ ተብየው ከሩቅ የሚለይባቸው ቀለሞቹ ናቸው፡፡
የሚቀያየሩ ከንቲባዎችም የከተማዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሳይሆኑ ሕግ እየተጣሰ እና አዲስ አፓርታይዳዊ ማሻሻያ እየተደረገ የመጡ ናቸው፡፡ ኦህዴድ/ብልፅግና የቀድሞውን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማን ወደ ስልጣን ሲያመጣ ድርጅቱ ባስቀመጠላቸው ርዕይ አፈፃፀሙን እንዲተገብሩ ነበር፡፡ አቶ ታከለ ተሳካላቸው ወይስ አልተተሳካ ለሚለው ክርክር በዚህ ፁሁፍ ለመዳሰስ ከጊዜ አኳያ አልፈዋለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የተጫኑት ታከለ ኡማ አዲስ አበባን የኦህዴድ እስር ቤት ለማድረግ ብሎም የሕዝብ ስብጥር ለውጥ ለማምጣት ብዙ ጥረዋል፡፡ በድርጅት መዋቅር የታገዘ ስራ ተከናውኗል፡፡ የሕዝብ ስብጥር ቅየራውን የወቅቱ የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ በአዲስ አበባ ውስጥ ጣልቃ ገብተው በነሲቡ አቀላጥፈውታል፡፡ ከሶማሌ ‹ክልል› ‹ተፈናቀሉ› ተብለው የመጡ ሰባት መቶ ሺህ ኦሮሞዎች እውን ተፈናቅለው ሳይሆን በለማ ትዕዛዝ ከሰላማዊ ኑሯቸው ተነስተው የመጡ ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሰዎች አረጋግጠናል፡፡ እንቅስቃሴውም የገዳን ወረራ በአዲስ አበባ ለማስጀመር ያለመ ነበር፡፡ ለዚህም ነው በአንድ አካባቢ ብቻ ራሱን የቻለ ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ መንገር በመንግሥት ተገንብቶ የተሰጣቸው፡፡ ዜጎች እውን ተፈናቅለው ከሆነ በዚያው በሶማሌ ‹ክልል› ቦታ የመስጠት ፍላጎት እንደነበራቸው የወቅቱ የአካባቢው ገዥዎች ጠይቀው እንደነበርም ግልፅ ነው፡፡ ይህ አዲስ አበባን ከመውረርም በተጨማሪ የሶማሌን ማሕበረሰብ ያለወንጀሉ ደም የመቀባት አባዜ ነው፡፡ በዚህ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ያልተናነሰ የሶማሌም ሕዝብ ተጎጂ ነው፡፡ ሕዝቡ አሁንም ይቅርታ ሊጠየቅና እውነታው ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡
የገዳ ወረራ
በኦህዴድ በጠላትነት የተፈራጀና መጤ የተባለ ሕዝብ በየሰበቡ ተፈናቅሏል፡፡ እየተፈናቀለም ነው፡፡ በአንፃሩ የልማት ተነሽ አርሶ አደር ልጆች በሚል ሽፋን ኦሮሙማን ለመትከል እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከልዩ ጥቅም በላይ የባለቤትነት ጥያቄው የህግ መሰረት እንዲኖረው ተረኝነት ያልተፃፈ ህግ እንዲሆን አቅም በፈቀደላቸው መጠን እየሠሩ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በአዲስ አበባ የተፈፀሙ አሁንም እየተሰራበት የሚገኘው የድሆች መፈናቀል ቤት ፈረሳ ከተማዋን በማስዋብ ስም ቀጥሏል፡፡ የቅርስ ፈረሳውም ሌላ ዘመቻ ነው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ከድሆች ነጥቆ ለወቅቱ የኦህዴድ ባለስልጣናት ማደል፣ ለተመረጡ ቄሮዎች ማከፋፈል የወረራው መገለጫዎች ናቸው፡፡ የስርዓቱ ዐይን አውጣነት የሚታየውም እዚህ ላይ ነው፡፡ የባልደራስ አመራሮች እስር ቤት የተወረወርነው የዚህ ወረራ ተከላካዮች በመሆናችን ነው፡፡
ድሃው ሕዝብ ከዕለት ጉርሱ ቆጥቦ የሠራው የጋራ መኖሪያ ቤት ለተመረጡ ግለሰቦች ሲታደል ከመቃወም የዘለለ የዳሰሳ ጥናቶች ተደርገው በርካታ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ በነበርንበት ወቅት ወደ እስር ቤት ብንመጣም እውነታው ግን ሊታሰር አልቻለም፡፡ በታከለ ኡማ መንበር የተተኩት የኦህዴድ ከንቲባ አዳነች አበቤ በ18/06/13 በኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ በባለሙያዎች ‹አስጠናሁ› ባሉት እና ስም ባወጡለት ዘረፋ 2695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በውቅቱ ዘራፊዎች እንደተያዙ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ንጥቂያ ተጠያቂ ያደረጉት የወቅቱ አመራሮችን ነው፡፡ ኦሕዴድ ሌባም፣ ከሳሽም፣ አጣሪም፣ ፈራጅም ራሱ የሆነበት ገጠመኝ፡፡
አቶ ታከለ ኡማ ከሓላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ 21 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለኦሮሞ ተወላጆች ማደላቸውን በኩራት ተናግረዋል፡፡ እቅዳቸው ለ65 ሺህ የኦሮሞዎች ገበሬዎች ማደል እንደነበርም ጨምረዋል፡፡ ታከለ እና የኦሕዴድ ጓዶቻቸው ራሳቸው ባመኑት መሠረት ቢያንስ በዚህ ወንጀል መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ አሁንም ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ፍርዱን ለታሪክ መተው ይሻላል፡፡ በአዳነች አቤቤ ሪፖርት መሠረት እንኳን ከጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል 5 ሺህ ያህሉ ለመንግሥት አመራሮች ብቻ ነው የተሰጡት፡፡ ይህ መንግሥታዊ ውንብድና ነው፡፡ ለየትኞቹ አመራሮች እንደተሰጠም ስም ተጠቅሶ መብራራት አለበት፡፡ ደላሎቹ እነማን እንደሆኑም ሪፖርቱ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቤቶቹን ሊመልሱ እና በሂደቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡
በአዲስ አበባ የሚደረገው የኦህዴድ መቆሚያ ያጣ ተረኝነት ድርጅቱ ከምርጫ ይልቅ ለውጊያ የተዘጋጀ በሚመስልበት በአሁኑ ጊዜ ፖለቲካው እንዳይረጋጋ አድርጎታል፡፡ ባለመረጋጋቱ ውስጥ ደግሞ የገዳ መንግሥታዊ ወረራ እየተስፋፋ ነው፡፡ በአዲስ አበባ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ እየተሰጠ ያለው የኦሮምኛ ትምህርትም የወረራው መገለጫ ተደርጎ ቢወሰድ ስህተት አይሆንም፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያን የመተልተሉ እንቅስቃሴ ለዚህ ማስፈፀሚያ ስልት የተቀየሰ ነው፡፡
መጪው ምርጫና አዲስ አበባ
የአዲስ አበባ ለአመታት የተወሳሰቡ ችግሮችና አስተዳድራዊ ጥያቄዎቿ በመጭው ምርጫ መልስ ያገኛሉ ብየ አስባለሁ፡፡ ሕዝቡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የፖለቲካዊ ውክልና ጥያቄ አለው፡፡ የኑሮ ውድነት ሰቀቀን ሆኖበታል፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግሮች፣ የሥራ አጥነት ጣጣ፣ የትራንስፖርት የትራንስፖርት ስቃይ በጥቂቱ የሚጠቀሱት ችግሮቹ ናቸው፡፡ አሁንም ችግሮቹ አድማስ አልፈው የሕልውና ጉዳይ ሆነዋል፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት ቤታቸው ውጡ የሚባሉት፣ እላያቸው ላይ ቤታቸው የሚፈርሰው፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ቆንጨራ የሚቃጣባቸው እና ከድንጋይ እስከ ቦምብ የሚወረወርባቸው አዲስ አበቤዎች ቀላል አይደሉም፡፡ ኗሪው የእኩል ተጠቃሚነት መብትም የለውም፡፡ ኦሮሞ ያልሆነ ሁሉ ሁለተኛ ዜጋ ሲሆን ዐማራ ደግሞ በግልፅ በጠላትነት ተፈርጆ እየተሳደደ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ ለዚህ መልስ የሚሰጥ አስተዳድር መሰየም ይኖርባታል፡፡ በቅርቡ ከ51 ሺህ በላይ ለጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው እድለኞች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከእለት ጉርስ ቆጥበው የደረሳው መኖሪያ ቤት አይናቸው እያየ ለኦህዴድ ተረኞች ሲሳይ ተደርጓል፡፡ መጭው ምርጫ ለአዲስ አበባ ወሳኝ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ሂደትና ውጤቱንም በአይነ ቁራኛ መከታተል ያስፈልጋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በገዛ ሀገራቸው ተገፍተው ሜዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ የቤት ተስፋቸው የቄሮ ውርስ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ አስሩም ክፍል ከተሞች፣ በ116 በወረዳወችና በ817 ቀጠናዎች ባዶ መሬት በጠራራ ፀሐይ ለወራሪ ቡድን በማደል በአንድ ጀንበር ቱጃር ሀብታም ሲፈጠር እያየን ነው፡፡ ከፊሎቹም የመሬት ንግዱን አጧጡፈውታል፡፡ አዲስ አበቤ እስከ ሃያ ዓመታት የኖረበት ቤት እላዩ ላይ ሲፈርስበት ‹መጤ› እና ‹ሰፋሪ› የሚል መለዮ እየተለጠፈበትም ጭምር ነው፡፡ ይህ ችግር ተደማምሮ ነው እኛም ወደ ፓርቲ ትግል የገባነው፡፡
እነዚህና መሰል ነገሮች እየተስፋፉ በመምጣታቸው በህዝብ እሮሮ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ተመስርቷል፡፡ ፓርቲያችን የልዩ ጥቅም ፍላጎት ችግሮችን በመንቀስ ስርዓቱን ለማሳየት በስፋት ተንቀሳቅሷል፡፡ ለመፍትሄው ህዝቡ እንዲዘጋጅ ሃቀኛ የፖለቲካ ዝግጅት በመፍጠር ብዙ ሰርቷል፡፡ በርካታ የታሪክ አሻራዎችን አስቀምጧል፡፡ መሰረታዊ የድርጅት ግንባታን ከወቅቱ ፖለቲካዊ አክቲቭዝም ጋር በማጣጣም ህዝብን ለማንቃት ተችሏል፡፡ ይህ ተግባር በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያልተለመደ ነው፡፡ የሕዝቡን ችግሮች አብረን በመቅመሳችንም ባልደራስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ህዝብ ልብ እንዲገባ አስችሎታል፡፡
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ ታከለ ኡማ አዲስ አበባን ዙሪያ አስከብበው ባሰማሩት ቄሮ የጥፋት ተልዕኮ ከሽመልስ አብዲሳ ጋር ማስፈፀማቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ አልፏል፡፡ በግለሰቡ ጥያቄ ሳይኖራቸው በተለዋጭ ሹመት ሚንስትር አድገውቸ ለሌላ ዝርፊያ አመቻችተዋቸዋል፡፡ ወደ ማዕድን ሚንስትርነት በተዘዋወሩ አፍታ የክፋት ጡንቻቸውን የሚድሮክ የወርቅ ኩባንያዎች ላይ አሳርፈዋል፡፡
ታከለ ከከንቲባነት ከተነሱ በኋላ በምክትላቸው የመጡት የኦህዴድ/ብልፅግና ቀዳማዊ እመቤት አዳነች አበቤ የድርጅታቸውን እኩይ ርዕይ እያስቀጠሉ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡
ኦህዴድ ተነስቶ ኦህዴድ መጣ፡፡ አዲስ አበባ ከታከለ ኡማ ወደ አዳነች አበቤ ተሸጋገረች፡፡ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ እየተባባሰ ያለው የኦሮሙማ መስፋፋትና አስደንጋጭ ወረራ ቀደም ሲል የተያዘ የኦህዴድ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደቀጠለ እንግሊዝ ኢምባሲ አካባቢ ያለው ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በመሆኑም በሀገራችንም ሆነ በከተማችን አዲስ አበባ ትውልዱን የመታደግ ሓላፊነት ከፊታችን እየመጣ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የአዲስ አበባ ችግር የሚፈታው በማዘጋጃ ቤት ሳይሆን በ4 ኪሎ እንደሆነ ባምንም የማዘጋጀት ቤትን 138 ወንበር መቆጣጠር የፕሮቶኮል ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጥያቄ መፍቻ ነው፡፡
የነዋሪው ሰላምና ደህንነት ማስጠበቂያ ነው፡፡ የዚህ ትውልድ አድዋ ነው፡፡ አዲሱ ታሪክ ብረት ማንገብ ሳይሆን የምርጫ ሰራዊት መፍጠር ነው፡፡ ህልውናውን በካርዱ ድምፅ በአደባባይ አብዮት ማሰጠበቅ ምርጫችን ሳይሆን ግዴታችን ጭምር ተደርጓል፡፡ ይህ ምርጫ በተለይ ለአዲስ አበቤ ነፃነቱን የሚያውጅበት ሕዝበ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምርጫ የተበታተነ ድምጽ ይዞ እንዳይመጣ ፖለቲካዊ ቅንጅቶች ተጠናከረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ የጀመርነው ጥምረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም ጥምረቱን ሊቀላቀሉ ይገባል፡፡
አዲስ የኃይል አስላለፍ ያስፈልጋል፡፡ በተመረጡ ሀሳቦች ላይ አብሮ መቀናጀት የህልውና ጥያቄው ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ መንግሥታዊውን የገዳ ወረራ መመከቻ መንገዱም አብሮነት ነው፡፡