ለእስር ያላት ብዕር (ርብቃ አብርሐም)
ከፅንሰት እስከ ልደት፣
ከእድገት እስከ እውቀት፤
ሰብዓዊነት እኩልትን – በመርህ ብትፅፍ፣
ለአንድነት ህብረት – ቆርጣ ብትሰለፍ፣
ሌብነት ጭቆናን – አድሎን ብትፀየፍ፣
ዘረኝነት ልዩነትን – የአንባገነንን ግፍ፤
በሰላም በታገለች፣
አምርራ በሞገተች፣
ዘብጥያ ተጣለች።
ለውይይት ድርድር – የቆረበች ታጋይ፣
ለሕዝቦቿ ታማኝ – ቃል ለምድር ሰማይ፤
ስነ-ልቦናዋ – ለትውልድ የሚተርፍ፣
ሰንደቅ ያነገበች – የነፃነት ደጃፍ፣
ለፅኑ ዓላማዋ – ህሊናዋ ማይነጥፍ፣
‹ክልል› ለምኔ – ኢትዮጵያን ብታገዝፍ፤
ቃሊቲ ወረደች፣
ቂሊንጦ ታሰረች፣
ሽብርተኛ ሆነች።
ለእስር ያላት ብዕር – ምታነባ ቀለም፣
ነብስ የማታጠፋ – የማታፈስ ደም፣
የተሠራን ሀገር – ጥላቻ ማታወድም፤
ከስለት ከሹለት – ከመሳሪያም በላይ፣
በሀሳብ ንፉጋን – ተፈርታ ምትታይ፤
የሽግግር ሰነድ – አስልታ በከተበች፣
የሕገ-መንግሥቱን – ጉድለት በነቀሰች፣
አስታራቂ ሀሳብ – ለውይይት ባለች፤
በኃይል ለመናድ – በግድ ተፈርጃ፣
ከወህኒ ቤት ዋለች – በፈሪ ጠመንጃ፣
ፍትህ ተነፈጋት – በስጋት ማስረጃ፣
ወይ የብዕር ፍርጃ፣
መጨረሻዋን እንጃ።
(ርብቃ አብርሐም፤ ከአውስትራሊያ)