ጦርነት የግድ ከሆነ !
የሀሰት ክስ እየተመሰረተብኝ በእስር ያሳለፍኳቸው ዓመታት ይኸው ዘንድሮ አሥራ አንድን ረግጠው አልፈዋል፡፡ በወራት መቁጠር ካቆምኹኝ እንደሆነ ቆይቻለሁ፡፡ እሥረኛውን ዓመት አሰልቼ መቶ ሃያ ሲሆንብኝ፣ ለእኔም ለአድማጩም ስለ ወራት ማውራቱ ይሻላል ብዬ ወሰንኹ፡፡ ያለቅጥ ከብዶ እንዲታይ አልፈልግም፡፡ ለዚህች ሀገር ዲሞክራሲ ከእኔ በላይ የከፍሉትን ሳስብ አንገቴን እደፋለሁ፡፡ አካላቸው የጎደለ፣ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉት ደግሞ አንደበቴን ይቆልፉታል፡፡
የአሥራ አንዱን ዓመታት እስር ያሳለፍኩት እየታሰርኩ እየተፈታኹ እንጂ፣ በአንድ ግዜ ቆይታ አልነበረም፡፡ በእስረኛ ቋንቋ “ተመላላሽ” እባላለሁ፡፡ ይኸኛው አሥራኛው እስሬ መሆኑ ነው፡፡ በአሳሪዎቹ አያያዝ ከሆነ፣ ይኸኛው ከዘጠኙ መሠረታዊ የሆነ ልዩነት አላየሁበትም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ስድስት እስሮች በአብዛኛው በፖሊስ ተደብድቤያለሁ፡፡ በመጀመሪያው እስር የምታቃጥል ጥፊ አቅምሰውኛል፡፡ ያቺ ጥፊ ቀስ ብላ ተገልብጦ ወደ መገረፍ (“ወፌ ላላ” ይሉታል እስረኞች) አድጋለች፡፡ በተለምዶ አባባል፣ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ ሆኖም፣ የእኔ መደብደብና መገፋት ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ከለብ ለብ የሚያልፍ አይደለም፡፡ እንዳላጋንን እሰጋለሁ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ የትህትና አበባል አይደለም፡፡ እውነታው ነው፡፡
ይህም ሆኖ፣ ይኸኛው እስር እንደ አዲስም የምቆጥረው ነው፡፡ በዘጠኙ እስሮች ለህዝብና ለሀገር ዋጋ የከፈሉትን —- የሞቱትን፣ የቆሰሉትን፣ የተሰደዱትን፣ የተገደሉትን —- በአደባባይ ክብር ስንነፍጋቸው አላስታውስም፡፡ ግፍ ስሪዎቹ ሳይቀሩ ግፍ የተቀበሉትን የሞራል ልዕልና ለመካድ ከመንገድ ወጥተው ሲባክኑ አላስተዋልኹም፡፡ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ የተዳከሙ ቢሆኑም፣ “ይሉኝታ”፣ “ጨዋነት” የምንላቸው ነገሮች ትዝ ይሉኛል፡፡
አሁን ነገሮች ተለዋውጠዋል፡፡ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን፣ ይህ ሁሉ “ነበር” ሆኗል፡፡ “አይነኬ” ብሎ ነገር ቀርቷል፡፡ ሁሉም ይንጓጠጣል፣ ይሾብፍታል፣ ይሳቅበታል፣ ይጣጣላል፣ ይዋረዳል፡፡ ይኸው በዚህ ዙር እስሬ የድርሻዬን ተቀብያለሁ፡፡ “ጀግና” ተብዬ አልቀረኹም፡፡ እሰዬው! ለሀገር፣ ለህዝብና ለእውነት የሚከፈለው ዋጋ በጨመረ ቁጥር፣ የመጨረሻው ፍሬ —-ዲሞክራሲ! አንድነት! —- ይበልጥ ጣፋጭ ነው የሚሆነው፡፡
ይህን ጉዳይ በዚሁ ብንዘጋው ምነኛ መልካም በሆነ፡፡ ግን ሌላ መዘዝ አለው፡፡ “ የጋራ ጀግና” እንዳይኖረን መደረጉ አንድ አደጋ ነው፡፡ “የጋራ ቁስል” እንዳይኖረን እየተደረገ መሆኑ ደግሞ፣ አደጋውን ይበልጥ ያሳድገዋል፡፡ ያለ ጋራ ጀግናም፣ ያለ ጋራ ቁስልም እንደ ሀገር መኖር አንችልም፡፡ ያንዣበበብን አደጋ በስሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ጦርነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡
ከሰሜን የጦርነት ቀጠናዎች —- ትግራይ፣ ዐማራና አፋር—- የሚወጡ ዜናዎች የጅምላ ግድያዎችና አስገድዶ መደፈሮች መፈፀማቸውን እያበሰሩን ይገኛሉ፡፡ የእኛ ምላሽ ምን ሆነ? ለሁሉም ሰለባዎች እንጀታችን ባባ? ለሁሉም ሰለባዎች የሀዘን አንገታችንን ደፋን? አላደረግነውም! “የማይካድራ ጭፍጨፋ አልተፈፀመም” ብለን ሽንጣችንን ይዘን የምንክድ ሰዎች፣ “የአክሱም ጭፍጨፋ ተፈፅሟል” ብለን ብራ ከረዬ ስንል ዓይናችንን አናሽም፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በአክሱም ጭፍጨፋ ስለመፈፀሙ መግለጫ ሲያወጡ አምርረን የምንከፋ ሰዎች፣ ስለማይካድራ ተመሳሳይ መግለጫ ሲያወጡ ከልብ እንፈነጥዛለን፡፡
የአንዱ ሞት የጋ ሞት፣ የአንዱ ቁስል የጋራ ቁስል፣ የአንዱ በደል የጋራ በደል፣ የአንዱ ውድቀት የጋራ ውድቀት መሆኑ አልታይ ብሎናል፡፡ እንዲሁም፣ ይባስ ብሎ፣ የአንዱ ሞት፣ ቁስልና በደል የእኛ ድል የሚመስለን በጣም በዝተናል፡፡ የህፃናትና የአረጋዊያን ሰቆቃ እንኳን ልባችንን አልጋራ ብሎናል፡፡ አሳሳቢ ነው – በእጅጉ አሳሳቢ፡፡
እኛ እኮ እንዲህ አልነበርንም! እኛ እኮ ይህ አይደለንም! መቼ ነው መተሳሰብና መተዛዘን ያቆምነው? እኛ እኮ በአንድ ጣራ ሥር የምንፀልይ፣ ለአንድ ሰንደቅ ዓላማ ህይወት እየሰጠን የኖርን፣ ለጎረቤታችን ደራሽ የሆንን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንደሰትና የምናዝን፣ ሰብሎቻችንን በአንድ አውድ የምንበላ፣ ልጆቻችንን በትዳር የምንገምድ፣ ሚሥጥሮቻንንና ህልሞቻችንን በአደራ የምንሰጣጥ፣ “አንተ ትብስ፣ እኔ እብስ” መባባልን የምናውቅ ህዝብ ነን፡፡ ይህንን ነው “ ኢትዮጵያውያን በኃይማኖት የተገራን ነን “የምንለው፡፡ ከዚህ ውጭ ያመጣነው ፈሊጥ የእኛ አይደለም፡፡ ባዕድ ነው፡፡
አሁን የሆነውን፣ የተጠናወተንን አባዜ አውቀነዋል? “የጠላት ወገንን ሳቆቃ አላይም፣ ስለመከራው አልሰማም አልናገርም” እያልን ብቻ አይደለም፡፡ የጠላት ወገንን ሰቆቃ ውሸት ነው ብለን ካልተከራከርን፣ ካልሳቅንበት፣ ካላጓጠጥነው የአእምሮ እረፍት ተስኖናል፡፡ እድሉ ከተገኘም፣ የጠላት ሬሳ ጎን ቆመን በሞባይላችን ሰልፊ ለመነሳት ወደ ኋላ የማንል ሆነናል፡፡ እንደ ሰው ልጅ፣ እንደ ሀገር ልጅ መተሳሰብና መተዛዘን አቅቶን ዓለም በአግራሞት የሚመለከተን ትራጅዲዎች ሆነናል፡፡
መለወጥ አብን፡፡ ለራሳችን ብለን መለወጥ አለብን፡፡ ሰብዓዊነታችንን፣ ህሊናችንን፣ ነፍሳችንን ለመታደግ መለወጥ አለብን፡፡ በየትኛውም ወገን ሆነን አጥብቀን የምንሻው ድል፣ ፈጣሪ ከሰጠን ህገ – ልቦና የሚበልጥ አይደለም፡፡ የተቀደሰን ዓላማ የኃጥያት መንገድ ያረክሰዋል፡፡ ይህ ነው የታሪክ አንኳር አስተምሮ። መንገዳችንን ለማስተካከል መለወጥ አለብን፡፡
ይህ ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ በጦርነቱ ያሉት ሁለቱ ተፋላሚዎች እኩል የሞራልና የፖለቲካ ዋጋ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ አንዱ ጋር እውነት፣ አንዱ ጋር ጥፋት አለ፡፡ አንዱ ወገን ጦርነቱን ለኩሷል፣ ሌላኛው ለመከላከል ተገድዷል፡፡ አንዱ ወገን ሀገርን ለማስቀጠል፣ ሌላኛው ለመበተን ይታገላል፡፡ የአንደኛው ጥላቻ ከሌላኛው የላቀ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ታሪክ በየትኛው በኩል እንደቆመም
እናውቃለን።
ግን ግን፣ ድል የሚገኘው በጦር ግንባር ብቻ አይደለም፡፡ ፍልሚያው ብዙ ግንባሮች አሉት፡፡ የአሻራ (legacy) ግንባር አለ፡፡ አሻራችን ከተለያዩ ወንጀሎች ንፁህ መሆን አለበት፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት – The end does not justify the means ። የልጆቻችን ግንባር አለ፡፡ ልጆቻችን በሞራል ልዕልናችን መኩራት አለባቸው፡፡ የህሊና ግንባር አለ፡፡ ህሊናችንን የሚኮሰክስ ነገር መኖር የለበትም፡፡ የታሪክ ግንባር አለ፡፡ መጪውን ትውልድ የሚያጨቃጭቅ ውርስ ማስተላለፍ የለብንም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ሁሉን የሚያወቀው፣ ሁሉን የሚስማው፣ ሚሥጥራችን ሁሉ የማይሰወርበት ኃያሉ ፈጣሪ ፊት ተጠያቂ ለመሆን የምንቆምበት ግንባር አለ፡፡ በእሱ ፊት ለምህረት እንኳን ብቁ ሆነን ካልተገኘን፣ ሁሉ ነገራችን ዜሮ ይሆናል፡፡
ጦርነት ባይኖር ይመረጣል፡፡ ጦርነት የግድ ከሆነ ግን፣ ፍትሃዊ ጦርነት ይሁን፡፡ ፍትሃዊ ጦርነት መተሳሰብና መተዛዘን ያለበት፣ ራህራሄን የሚያወቅ፣ ጥላቻ፣ በቀልና አዋራጅነት የሌለበት ነው፡፡ ጦርነት የግድ ከሆነ፣ ለሰላምና ለፍቅር የሚደረግ ጦርነት ይሁን። ጦርነት ለማስቀረት የሚደረግ ጦርነት ይሁን፡፡
እስክንድር ነጋ፣ የፖለቲካ እስረኛ ከቂሊንጦ