ዋልጌ ዳኞች! ጌጥዬ ያለው
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ (5 ሰዎች) ላይ በከፈተው ዶሴ ያሉትን የሰው ምስክሮች እንዲያሰማ አዝዟል። በመሆኑም ሀምሌ 8፣ 9፣ 14፣ 15 እና 16 ቀን 2013 ዓ.ም. 21 ምስክሮችን በግልፅ ችሎት እንዲያቀርብ ተወስኗል። በዚሁ መሰረት ቢጠበቅም ዐቃቤ ሕግ (ዐቃቤ መንግሥት) የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቀናት ምስክር ያሳቀርብ ብቻውን ቀረበ። ከዚህ ቀጥሎ አምስቱንም ቀናት ብቻውን ቢቀርብና ማስመስከር ባይችል ኖሮ በሌላ ጊዜ መልሶ የማንቀሳቀስ መብቱ ተጠብቆለት ለጊዜው ክሱ ተቋርጦ መዝገቡ ይዘጋ ነበር።
የነፃነት ታጋዮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌም ከእስር ይፈቱ ነበር። ሆኖም በሦስተኛው ቀን ማለትም ሀምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ዐቃቤ መንግሥት ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው በሌሉት አስወስኖ የእግድ ደብዳቤ ይዞ ቀረበ።
ሃምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ‘ምስክር አሰማ የምባል ከሆነ ፍትሕ ይጓደላል’ ሲል ያቀረበውን አቤቱታ በፊርማቸው ይዘው ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረቡት ተመስገን ላጲሶና ደመላሽ ኢጀታ ናቸው። ተመስገን ላጲሶ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ ወንጀሎች ዳይሬክተር ነው። ይህ ሰው ከጀርባ ቢኖርም ለችሎቶች ግን እንግዳ ነው። #አብይ መርዕድ የተባለው የአምቦ ተወላጅ ‘እንደዚህ አይነት የሀሰት አቤቱታ አላቀርብም። አልፈርምም’ በማለቱ ነው ተመስገን የመጣው። አብይ መርዕድ በዚህ ባህሪው ለባልደረቦቹ ቤትና መኪና ሲሰጥ ዳረንጎት እንዳልደረሰውም ሰምቻለሁ።
ይኸው ነው፤ በጥቅማጥቅም እየተደለለ የሚፈርድና የሚከራከር ባለሙያ ሲጠፋ አለቆች ይመጣሉ። ሁሉም አሻፈረኝ ቢሉ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተብየ)፣ ብርሃነ መስቀል ዋቅጋሪ (የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ተብየ) እና መዓዛ አሸናፊ (የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ተብየ) ይመጣሉ። ሦስቱም እምቢ ቢሉ የውንብድና ስርዓቱ ተንኮታኩቶ እስካልጠፋ ድረስ ከሳሽም ፈራጅም ሆኖ አብይ አሕመድ ራሱ ካባ ደርቦ መምጣቱ አይቀሬ ነው።
የዐቃቤ ሕግን አቤቱታ ተቀብለው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሦስት ዳኞች ማለትም ሸምሱ ሲርጋጋ፣ ዋዚሞ ዋሲራ እና ደረጀ አያና አፀደቁት። በመሆኑም ሀምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ዐቃቤ ሕግን በምስክሮች ፈንታ የእግድ ደብዳቤ አስይዘው ወደ እስር ፍርድ ቤቱ ላኩት። የእስር ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 260175 ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ያሳለፈው ውሳኔ ታግዶ ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተመለሰ።
የእነ ሸምሱ ሲርጋጋ ችሎት በዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ላይ የጠበቆችን መልስና የመለስ መልስ በፅህፈት ቤት ለመቀበል ለሀምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። መቼም መለዋወጥ ዋነኛ መገለጫቸው ሆኗል። በዚሁ መሰረት የእነ እስክንድር ጠበቆች አስቀድሞ እንደታዘዘው በፍርድ ቤቱ ፅህፈት ቤት ተገኝተው የዐቃቤ ሕግን አቤቱታ ለማየትና መልስ ለመስጠት ቢጠይቁም ተከለከሉ። ‘ለተከሳሾች ለራሳቸው እንጂ ለጠበቃ አንሰጥም’ በሚል ተባረሩ። ፍርድ ቤቱ እነ እስክንድርን ጠበቃ አልባ ለማድረግ ሞከረ።
እስረኞች የማይቀርቡበት የሀምሌ 26ቱ ችሎት ለዛሬ ነሀሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀጠረ። ነገር ግን ዛሬም መዝገቡ ሳይገለጥ ለነገ ነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። ከላይ የተጠቀሱት ሦስት አውታታ ዳኞች ለዚህ የሰጡት ሰበብ “መዝገቡን አልመረመርንም” የሚል ነው። ለመሆኑ ምን እየሠሩ ነው ያልመረመሩት? ሥራን ያለ መሥራት ዋልጌነት ሊያስቀጣስ አይገባም ወይ? በእነርሱ ዋልጌነት አራት ንፁሃን ዜጎች ፤ ያውም ኢትዮጵያ ላለችበት ወቅታዊ ችግር ከፍተኛ የመፍትሔ አመንጭነት አቅም ያላቸው ታላላቅ ፖለቲከኞች እስር ቤት መቆየታቸው አያሳስባቸውም ወይ?
ከዚህ በፊትም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ‘መዝገቡን አልመረመርኩም፣ ዳኞች ተሟልተው አልቀረቡም፣ ፕላዝማ ተበላሽቶብኛል’ በማለት ችሎቶችን ሲያጓት ቆይቷል። የወንበዴ ጥላ ከለላ ሆኖ ንፁሃንን ማንገላታት እስከ መቼ?