ወ/ሮ መሶበወርቅ ቅጣው፤ በባልደራስ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሕዝባዊ ውይይት ላይ ያደረጉት ንግግር
ክቡር አቶ አምሀ ዳኘው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ ክቡር ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የተከበራችሁ እጅግ የምናከብራችሁ ደጋፊዎቻችን እና የፓርቲያችን አባላት በቅድሚያ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ የፓርላማ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት እጩዎቻችንን ለመተዋወቅና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ጥሪያችንን አክብራችሁ በመምጣታችሁ በራሴና በባልደራስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ዛሬ ሀገራችን እጅግ በጣም ውስብስብ በሆኑ ከፍተኛ ችግሮች ተተብትባ በመቃተት ላይ የምትገኝበት ጊዜ ነው፡፡ እውነተኛ የሆኑ አገር ወዳድ ዜጎች የኢትዮጵያ ስቃይ ስቃያቸው፣ ችግሯ ችግራቸው፣ መከራዋ መከራቸው በመሆኑ ከገባችበት አዘቅት ለማውጣ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ መገደል፣ መፈናቀል፣ መታሰር፣ የኑሮ ውድነት መናር፣ መራብ፣ መታረዝ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድና የመናገር መብቶች መነፈግ፣ ከቦታ ወደቦታ በሰላም መንቀሳቀስ አለመቻል እና መሰል ችግሮች የዕለት ከዕለት ኑሯችን ሆነዋል፡፡ ዛሬ ህወሃት በሥልጣን ላይ ባይኖርም እሱ ያዘጋጀው ሰዎችን በዘር አለያይቶ የሚያባላውና ሃገርን የሚበታትነው ህገ መንግሥት ግን በኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ወይም በብልጽግና ፓርቲ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ጽንፍ የረገጡ አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ወያኔ ከሚፈጽማቸው ተግባራት በባሰና ይሉኝታ በሌለው መንገድ ሁሉም የእኛ – ኬኛ በማለት ቤቶችን እና መሬትን እየተቀራመቱ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ከላይ እስከታች ያሉ ቁልፍ የሥራ ቦታዎችን በአንድ ዘር ያስይዛሉ፡፡ ጠቃሚ የገቢ ማስገኛ ተቋማትንም እንደዚሁ በቁጥጥራቸው ሥራ ያውላሉ፡፡ ዜጎች በማንነታቸውና በሀይማኖታቸው ምክንያት በገጀራ ሲቆራረጡ፣ በቢላዋ ሲታረዱ፣ ሆዳቸው በስለት እየተሰነጠቀ ጽንሶች በሜዳ ላይ ሲጣሉ፣ አስከሬኖች እንደአልባሌ እቃ እየተወረወሩ በአንድ ጉድጓድ ሲቀበሩ፣ ንብረቶቻቸው ሲዘረፉ፣ ቤቶቻቸው በእሳት ሲጋዩ፣ ቤተ እምነቶቻቸው ሲቃጠሉ እና ሌሎችም ከፍተኛ ሰቆቆ ሲፈፀምባቸው ሰላማቸውን የመጠበቅና መብታቸውን የማስከበር ግዴታ ያለበት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ አዲስ አበባ ላይም ‹‹ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይገባናል›› ከማለት አልፈው ‹‹በአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት አለን›› በማለት ከፍተኛ በደል እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ዘረኛ አስተሳሰባቸውን በመቃወም ፍትሃዊ ሥርዓት ለማስፈን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ‹‹አዲስ አበባ የኗሪዎቿ ናት፡፡ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን ናት፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ናት፡፡ በአዲስ አበባ የተወለዱና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተወልደው በከተማዋ የሚኖሩ እኩል ባለመብቶች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በራሷ ልጆች መመራት አለባት፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውህድ ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡›› የሚል መርህ ይዞ በመነሳት ሕዝቡን በማታገል ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች ጋር በማስተር ፕላን ልትተሳሰር ይገባል፤ የከተማዋ ነዋሪዎችም በዙሪያዋ ባሉ ቦታዎች ያለምንም መሸማቀቅ ቤት የመሥራት እና የንግድ ተቋማትን የማቋቋም የዜግነት መብታቸው ምንም ሳይሸራረፍ ሊጠበቅላቸው ይገባል ብሎ ባልደራስ ያምናል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አምባገነንነትን፣ ዘረኝነትን፣ ግለኝነትን፣ አድሎአዊነትን፣ አሉባልተኝነትን እና ቡድነኝነትን ይዋጋል፡፡ በአሁን ወቅት በእስር ላይ የሚገኘው እስክንድር ነጋ ለባልደራስ መመሥረትና መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የፈጸማቸው አኩሪ ተግባራት በድርጅቱ አባላት፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ እንዲኖረው አድርገውታል፡፡ ዛሬ እያካሄድን ያለው ትግል የሞት የሽረት ወይም የመኖር ያለመኖር መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል፡በኦሮሞ ብልጽግና እየተመራ ያለው ኢህአዴግ ቁጥር 2 የአዲስ አበባን ሕዝብ በእንጀራ ልጅነት እየተመለከተ የተለያዩ በደሎችን እያደረሰበት ይገኛል፡፡ በርካታ ወጣቶች ተምረው በአደጉባት ከተማ የበይ ተመልካች ሆነው አለሥራ ተቀምጠዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ግብር እየተጣለባቸው ከመስኩ ወጥተዋል፡፡ ብዙ ኗሪዎች ቤት በላያቸው ላይ እየፈረሰባቸው ቤት የለሽ ሆነዋል፡፡ ኗሪዎች የኮንዶሚንየም ቤት ለማግኘት ለዘመናት ገንዘብ በባንክ ቢቆጥቡም የቤት ባለቤትነት ዕድል ለአንደኛ ደረጃ ዜጎች እንጂ ለቆጣቢዎቹ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ አዲስ አበቤ የተነፈጉትን መብቶቹን ለማስከበር ማንን መምረጥ እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል ብለን እናምናለን፡፡ በሃገርና በሕዝብ ላይ በደል እያደረሰ ያለውን አስከፊ ሥርዓት በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመተካት ምርጫው ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ባልደራስ በእጅጉ ያምናል፡፡ የምርጫ ካርድ አምባገነኖችን ከስልጣናቸው እንደሚያወርዳቸው እንደምትገነዘቡም ይረዳል፡፡ በመሆኑም እናንተ ደጋፊዎቻችን ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ቤተሰቦቻችሁን፣ ጓደኞቻችሁን እና ወዳጆቾቻችሁን ሁሉ በማስተባበር በነቂስ ወጥታችሁ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን እንድትመርጡ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡ ምርጫው እንዳይጭበረበርም በትኩረት እንድትከታተሉ እናሳስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!!
ድል ለዲሞክራሲ!!!