ከስራቸው የተፈናቀሉ ሰራተኞች በአስቸኳይ ወደ ስራ ገበታቸው ይመለሱ

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአንበሳ አውቶቡስ እና የኢትዮ ፖስታ አገልግሎት ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤት ሰራተኞች በግፍ ከስራቸው እየተባረሩ መሆናቸውን ባልደራስ ከደረስው የህዝብ ቅሬታ አረጋግጧል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንት ብቻ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ከ480 በላይ ሠራተኞች አለ አግባብ ከስራቸው ሲባረሩ ፣ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ደግሞ እንደዚሁ ተመሳሳይ 450 በላይ ሰራተኞች ተባረዋል፡፡ ለፓርቲያችን የሚደርሱት የሕዝብ ጥቆማዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ምን አልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የመንግሥት ሰራተኞች ብሔራቸውን በመጥቀስ ፎርም ሞልተው የብቃት መመዘኛ በሚል ፈተና መሰጠት ሲጀመር ፣ሆነ ተብሎ የአማራ ተወላጆችን እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከስራ የማፈናቀል ተግባር መሆኑን አጋልጠናል፡፡‘’የብቃት መመዘኛ‘’እየተባለ የሚሰጠው ፈተና ለዓመታት ብቸኛ መፈተኛ ቋንቋ ሁኖ ሲያገለግል በቆየው የአማርኛ ቋንቋ ተፈትነው በአንድ መስሪያ ቤት ሲሰሩ የኖሩ ሰራተኞችን ፣በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲፈተኑ የተደረገበት ስልታዊ የማባረሪያ ምክንያት ነበር፡፡ በተጨባጭ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከስራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉት አብዛኞቹ በአማርኛ ቋንቋ ፈተና የወሰዱት ናቸው፡፡
በነገድ ላይ የተመሰረተው አገዛዝ ሆነ ብሎ የአንድን ማሕበረሰብ አባል ለማጥቃት የሚጠቀምበት መሳሪያውም የብሔር ብረሰቦች እና ሕዝቦች የሚባለውን’’ ሕገ መንግሥት’’ ነው፡የኦሕዴድ/ኦነግ/ ብልፅግና ፖለቲከኖች የፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤት ‘’በአንድ ማሕበረሰብ ተይዟል’’ በሚል ሲለፉት የነበረውን የጥላቻ አካሄድ ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ በዚህ ኢ ህገ – መንግሥታዊ አካሄድ የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨምሮ የአማርኛ ቋንቋ ተናገሪውን ሕዝብ ግንባር ቀደም የጥቃቱ ሰለባ አድርገዋል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ በሀገር እና በሕዝብ ላይ ከባድ መከራን ከማስከተል እና ሀገርን ከማውደም የዘለለ ለማንም ቡድን ወይንም ግለሰብ የሚሰጠው ዘላቂ ጥቅም አይኖርም፡፡
ባልደራስ ለአውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ለአስርት ዓመታት ያገለገሉ ሰራተኞች እና ቤተሰቦቻቸውን ጎዳና ላይ የሚጥል ውሳኔ በአገዛዙ መሰጠቱን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ፓርቲያችን ባልደራስ በዚህ የግፍ ውሳኔ ተጠቂ የሆኑ ወገኖቻችን ፍትሕ እንዲያገኙ እና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ አሰራሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል።
- በግፍ ከስራቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ እናሳስባለን፤
- ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከስራቸው ከተባረሩ ዜጎች ጎን ቁሞ ሰላማዊ ተቃውሞ እንዲያሰማ ጥሪ እናቀርባለን፤
- ከስራቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለሚያደርጉት ማንኛውም ሰላማዊ ተቃውሞ ፓርቲያችን ሙሉ ድጋፉን ይሰጣል፤
- የሚመለከታችሁ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ የምትስሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሚዲያ አካላት የመስራት መብት በፈረንጆች አቆጣጠር በ1966 በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የፀደቀው የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (United Nation Universal Declaration of Human Rights) (UNDHR)በአንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ አንድ (1)ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን የዜጎች መብት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ ፣የማሕበራዊ እና ባህላዊ መብቶች (The International Covenant on Economic, Social and Cultural Rights) (ICESCR) ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተተውን መሠረታዊ መብት ግልፅ በሆነ ሁኔታ የሚጥስ በመሆኑ ፣ይህን ህገ ወጥ ድርጊት ለዓለም በማጋለጥ ለመብቶች መከበር እየተደረገ ላለው ሀገራዊ ትግል የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ እና የሰላማዊ ለውጡ አካላት በሙሉ የዜጎችን ከስራ መፈናቀል በፅኑ በመቃወም የሰላማዊ ትግሉ አካል እንድትሆኑ ፓርቲያችን ባልደራስ አበክሮ ይጠይቃል፡፡
የባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

