እስር ቤት፤ ደርሶ መልስ
(ጌጥዬ ያለው)
የገዥው ፓርቲ የጎበዝ አለቃ (በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫና የምርጫ ስነ ስርዓት አዋጅ መሰረት በጉባኤ ያልተመረጠ) አብይ አሕመድ እንዳልተቀባ ንጉስ ድንገት ሥልጣን ላይ ጉች ካለ በኋላ ሆይ ሆይታው ብዙ ነበር። ሆኖም የጫጉላ ሽርሽሩ ከአንድ የጎጃም መኳንንት ሰርግና ምላሽ የበለጠ ጊዜ አልወሰደም። ከዓመት ባነሰ ጊዜ እውነቱ ተገለጠ። እውነተኛ ማንነቱን ከሕዝብ ለመደበቅ የስለላና የደህንነት ሙያው እምብዛም አልጠቀመውም ማለት ይቻላል።
የማይሰለቸው ፅኑ የነፃነት ታጋይ #እስክንድር ነጋ ብቅ አለና አስለፈለፈው። ‘ሙሴ’ ያሉት ሰው ሰዎችን በጅምላ ገድሎ፤ በነሲብ የሚቀብር ጨፍጫፊ ሆነ።
የጎበዝ አለቃው ከኤርትራ ጋር የነበረውን ቁርሾ ከልቶ አንድነት ሲፈጥር፤ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሽርክ ሲሆን ዓለም በአድናቆት ዘግቦታል። ወቅቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሜክሲኳውያን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የግንብ አጥር ለማሳጠር ያወጀበት ነበርና “አሜሪካ ላይ የጥል ግንብ ሲገነባ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የፍቅር ድልድይ ተሠራ” እያሉ በተለይ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በንፅፅር ዘግበውታል።
በተመሳሳይ #የአብይ አሕመድ የጫጉላ ሰሞን ሳይደበዝዝ የዓለም የፕሬስ ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል። በዕለቱ ተዘግተው የነበሩ ገፀ ድሮች ተከፍተዋል፣ ሕትመታቸው ተቋርጠው የነበሩ ጋዜጦችና መፅሔቶች ዳግም ወደ ሥራ እንዲመለሱ በር ተከፍቷል፣ ስደተኛ የነበሩ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃን ተመልሰዋል ወዘተ በሚል በዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (CPJ) ጭምር ተመስግነዋል። በርግጥ በዓሉ የተከበረው በመንግሥት እና በሕዝብ ግንኙነት ሠራተኞቹ እንጂ በጋዜጠኞች ነበር ለማለት ያስቸግራል።
የሆነው ሆኖ የአዲስ አበቤው እስክንድር ነጋ እንቅስቃሴ የአብይ አሕመድን ጸረ አንድነት፣ ጸረ ዴሞክራሲ፣ ጸረ ታሪክ፣ ጸረ ቅርስ ከሁሉም በላይ ጸረ አማራ ዛር አውርዶ አስለፍልፎታል። ግልፅ ጦርነት ከማወጅም ባለፈ “ታስሮ ጀግና መሆን የሚፈልግ ጋዜጠኛ ነው ያለው” ተባለ። ይህ አደገኛ ንግግር ነው፤ ጥቂት የማይባሉ ጋዜጠኞችን እንዳይፅፉና እንዳይናገሩ አሸማቋል። ቅቤ አንጓች ጋዜጠኞችም እንደ ውዳሴ ማርያም በነጋ በጠባ ደጋግመውታል። በአንዳንድ የግል መገናኛ ብዙሃን፤ አርታኢዎች ዘጋቢዎችን አንገት የሚያስደፉበት መከራከሪያ ብሎም የየማለዳ ስብሰባዎች (Morning briefing) መክፈቻ መሆኑንም ሰምቻለሁ። ንግግሩ የቤተ መንግሥቱን አጥር ተራምዶ ፎቶ ግራፍ መነሳትን እንደ ታላቅ የጋዜጠኝነት ጀብዱ ከሚቆጥሩና ጆሴፍ ፑልቲዘርን የሆኑ ከሚመስላቸው የጋዜጠኝነት ደናግላን አንደበት ላይም አይጠፋም።
ጠቅላይ ሚንስትር ተብየው አምባገነናዊ ዘረኛ ሥልጣኑን የሚያስጠብቅባቸው ሦስት መሰረታዊ ሃይሎች አሉ። 1ኛው ወታደራዊ ሃይሉ ነው። 2ኛው የስለላ መዋቅሩ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “የማሕበራዊ ሚዲያ ሰራዊት” የሚሉት ቅልብተኛ ፌስቡክ ጎርጓሪ ነው። 3ኛው የሥልጣን ማስጠበቂያ ሃይል አዲስ አሰላለፍ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ቅርፁና አቀራረቡ ይለያይ እንጂ ነባር ነው። በትነግ ጊዜ ‘ዲጅታል ወያኔ’ በሚል መጠሪያ በቅርፅም ሆነ በአደረጃጀት ሳይለይ ይኸው ራሱ ነበር፤ አለም። በነገሥታቱ ጊዜም ቴክኖሎጂው ስላልነበር እንጂ ድርጊቱ ሥራ ላይ ውሏል። ሕዝባዊ ቅቡልነት የጎደላቸው መሪዎች ሲነግሱ ሀሰተኛ አፈ ታሪኮችን ያስነግሩ ነበር። ለእረኞችና ለአዝማሪዎች ግጥም እየተሰጠ መወድሰ ንጉስ እንዲስፋፋ ይደረጋል።
ጋዜጠኞችን ወደ ሚያሸማቅቁበት ፍረጃ ልመለስ፤ በየሀረጉ አዝማች እየከፈቱና እየዘጉ የጎበዝ አለቃውን አሸማቃቂ ንግግር ደጋግመው የሚያዜሙት በ3ኛው የዘረኛ ሥልጣን ማስጠበቂያ ፈርጅ የተሰለፉት ፌስቡክ ጎርጓሪዎች ናቸው። እኔም ይህን የእስር ጉዳይ ስፅፍ ‘ጀግና ለመባል ነው የታሰርከው’ የሚል ቢኖር ‘ጀግንነት ጥሩ ነውና አብረን እንጀግን’ ብል ኢ- ግብረ ገባዊነት የሚያስብል አይመስለኝም።
እንኳንስ ትርጉሙ ረክሶ ለመላጣውም፤ ለጎፈሬውም የተናኘው ጀግንነት ጥቂቶች ብቻ የሚታደሉት እውነተኛው ጀግንነትም ከወህኒ ቤት የሚገኝ ቢሆን መከራው ብዙ ነው። በዚህ መልኩ ሊያገኘው የሚፈልግም ያለ አይመስለኝም።
የወህኒ ቤቶቻችንን አስከፊነት የዜግነት ማህበራዊ ዋስትናቸውን ተነጥቀው በጓዳና የሚኖሩ ወንድሞቻችን ይነግሩናል። ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ነፋሱን፣ አቧራውን፣ ርሀቡን ጥሙን ተቋቁመው በጎዳና ሲኖሩ በአንዳንድ ወንጀሎች ተጠርጥረው እስር ቤት ይገባሉ። ቤት፣ ምግብና ልብስም በእስረኛ ወግ ያገኛሉ። ሆኖም የተሟላ ኑሮ ካለው እስረኛ እኩል የመፈቻ ጊዜያቸውን በጉጉት ይጠብቃሉ።
መታሰር የሚያጀግን ቢሆን ኖሮ ያጀግናል ባዩ ራሱ ከምኒልክ ቤተ መንግሥት ወጥቶ ቃሊቲ በተገኘ ነበር። እስረኞች ጀግና የሆኑት ለመርህ ቆመው ወንበዴን በመታገላቸው እንጂ እጃቸው ውስጥ ሰንሰለት ስለገባ አይደለም።
#እስራት (አምና)
በገዳ ማሕበር ርዕዮተ መንደር እንደሚመራ የገለፀው የአብይ አሕመድ ቡድን ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ሦስት ጊዜ አስሮኛል። ሦስቱም በአማካኝ በየአንድ አመት ልዩነቶች የተደረጉ ናቸው። በመጀመሪያው በግልፅ የተነገረኝ ወይም የቀረበብኝ ክስ አልነበረም። ከቀላል ማስፈራሪያነት የዘለለ አልበረም። የአቤ ጉበኛን ሀውልት እያየሁ አድጌ፤ ከእስክንድር ነጋ ጋር እየኖርኩ ወንበዴን ብፈራ ታሪክስ ይቅር ይለኝ ይሆን?
2ኛው ባለፈው ዓመት በተከበረው ‘ኢሬቻ’ የሚሉት የጣኦት አምልኮ ቀን ዋዜማ ላይ የተፈፀመ ሲሆን ክሱ በመርማሪ ፖሊሱ በቢሮ ውስጥ ተነቦልኛል። ወንጀል የተባሉትም 1ኛ. ‘መሪ አልባው የአማራ ሕዝብ’ በሚል ርዕስ በፍትሕ መፅሔት የፃፍኩት መጣጥፍ ነው። 2ኛ. የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን (ባልደራስ) ቢሮ በመጠቀም ወጣቶችን ለሽብር ማደራጀት የሚል ነው። ሦስት ሲቪል ለባሽ ፖሊሶች ቃሊቲ፤ አውቶብስ መነኻሪያ አካባቢ ከሚገኘው የባልደራስ ቢሮ ውስጥ አግኝተው በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው የፖሊስ መምሪያ ከወሰዱኝ በኋላ የተረከቡኝ ፖሊሶች ስለተጠረጠርኩበት ወንጀልም ሆነ ስለ እኔ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ያመጡኝ ፖሊሶችም የአንድ ደህንነት ስም ጠርተው በእርሱ ትዕዛዝ ማምጣታቸውን ከመግለፃቸው ውጭ የነገሯቸው መረጃ አልነበረም። ከአንድ ጠባቂ ወታደር ጋር ቢሯቸው በር ላይ ረፋድ 5 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ተቀምጨ የሚፈታኝም፤ የሚያስረኝም ጠፋ። የቀኑ ፈረቃ ፖሊሶችና ሌሎች ሠራተኞች ወጥተው የማታ ፖሊሶች ተተኩ። እስረኛ አልተባለም እንጂ ጠባቂየም ከሥሬ ንቅንቅ አላለም። ስልክ እየደወለ ‘ኑ ተቀበሉኝ’ በማለት ይነጫነጫል። በዚህ መሃል አንድ መርማሪ ፖሊስ ተገዶ ቃሌን እንዲቀበልና እንዲያስረኝ ታዘዘ። እንዳላመልጥ ሲጠብቀኝ የዋለው ወታደርም ተልዕኮውን ጨርሶ ከፖሊስ ጣቢያው ወጣ። መርማሪው ካመጡኝ ፖሊሶች የተቀበለውን የፍትሕ መፅሔት ቅጂ የሽፋን ገፆች እያገላበጠ እያየ “ምንድን ነው የፃፍከው?” አለኝ።
“አማሮች እየተመረጡ በጅምላ እየተገደሉ ነው። ከጅምላ ጭፍጨፋዎች መካከል በቅርቡ በመተከል የተፈፀመውን የሚተርክ መጣጥፍ ነው የፃፍኩት። ይህ ሕዝብ በየቦታው የሚጨፈጨፈው መሪ ስለሌለው ነው ብየ አስባለሁ” አልኩት። የሚበቃውን ያህል ትንሽ ትኩር ብሎ መፅሄቱን አየው። ወደ ውስጥ ገፅ ገብቶ ግን አንድም አንቀፅ ሲያነብ አላየሁትም። ለረጅም ሰዓት የጠረንጴዛው የውስጥ ተሳቢ ኪስ ውስጥ ስለነበር የተከሰስኩበትን ፅሁፍ በደንብ አንብቦት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ።
“ወጣቶችን ለሽብር አደራጅተሀል” መባሌን በተመለከተም ለሕጋዊ የፖለቲካ ትግል ከማደራጀቴ በቀር አንዳች የጥፋት እንቅስቃሴ አለማድረጌን አስረዳሁ።
ቀጥሎ ባልተስተካከለ ሁኔታ (Unconditionally) ከመርማሪው ቢሮ ወጥቼ ወደ ጠባቧ የእስር ክፍል ገባሁ። የዚህ ክፍል የሌሊቱ ተረኛ ሓላፊ “ባልተሟላ የአስተሳሰር የመረጃ ጥንቅር (Unconditionally) አላስርም” በማለቷ
ከመርማሪው ተቀብሎ ከወሰደኝ ሌላ ፖሊስ ጋር ትንሽ ተከራከሩ። የክርክሯ ትርጉም የገባኝ በጧት ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡኝ ስጠይቅ ነው። ከፖሊስ ጣቢያው የተለመደ የአሠራር ደንብ ውጭ ባልተሟላ ሁኔታ የታሠርኩት እዚያው ታግቼ ሰንብቼ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ክስም ሳይመሰረትብኝ በነፃ እንድለቀቅ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ በመወሰኑ ነው። ለአምስት ቀናት ያህል ቃሊቲ ፖሊስ መምሪያ ስሰነብት መጀመሪያ ከጠየቀኝ መርማሪ ፖሊስ በተጨማሪ የተለያዩ የፖሊስ ሓላፊዎች እየተመላለሱ ስለመፅሔቱና ስለ ፅሁፉ ጠይቀውኛል። ከባልደራስ ጋር ስለተያያዘው ጉዳይ ግን እምብዛም አላነሱም። አንዳንድ ጥያቄዎቻቸው ተመስገን ደሳለኝን እንጂ ለጋዜጠኝነትም ሆነ ለፖለቲካ ለጋ የሆነ አምደኛን ያልያዙ አስመስለዋቸው ነበር። ለአብነትም “የመፅሔቱ የገቢ ምንጭ ምንድን ነው? የሚል ይገኝበታል። መልሴ “እኔ ምን አውቄ” የሚል ነበር።
ልፈታ ሰዓታት ሲቀሩት አንድ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ እንደሆነ የነገረኝ ሰው አነጋገረኝ። ኮፍያ ያደረገ፣ ወፍራም ጃኬት የለበሰ ሲሆን የተረጋጋና ቀይ ነው። ከንግግሩ አንዳንድ ድምፀቶቹ የትግርኛ ቋንቋ ተፅዕኖ ያለው ቢያስመስለውም ትግርኛ ተናጋሪ ለመሆኑ ርግጠኛ መሆን አልቻልኩም። ከአስመራ ለአብይ አሕመድ የተሰጠ ዳረንጎት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ባለመግባባትና በጦፈ ክርክር በግምት ለ2 ሰዓታት ያህል ተነጋግረናል። ይሄኛው የባልደራስን ጉዳይ ፈፅሞ አላነሳም። ረጅም ሰዓት ወስዶ የተናገረው ኢትዮጵያ እሳት ውስጥ እንደሆነችና ከእሳት ለማውጣት ከመንግሥት ጋር መተባበር እንደሚገባ ነው። በተለይም እሳቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ እንደማይገባ እያስረዳኝ ብዙ ደቂቃ ወስዷል። የእኔ ሃሳብ ‘እሳት ሆኖ እየፈጃት ያለው ራሱ መንግሥት ነው’ የሚል ነበር። በዚህ ጉዳይ ስንሟገት ነው ጊዜውን የጨረስነው። የማታው አዳሬ ሰላማዊ ስላልነበር ውስጤም ሆነ ውጫዊ ገፅታየ በቁጣ የተሞላ ነበርና አቋሜን ያለአንዳች ማለዘቢያ እንድገልፅ ረድቶኛል። በመጨረሻም እንድፈታ ፖሊሶችን አዝዞ ሄደ። ነገር ግን የፖሊስ መምሪያው ሓላፊ ነው መፍታት ያለበት ስለተባለ እሳቸው እስኪመጡ ረፋድ ላይ መፈታት ስችል እስከ ቀኑ አስር ሰዓት ገደማ ለመቆየት ተገደድኩ። በዚህ ጊዜም ‘ኢሬቻ እስከሚያልፍ አስራችሁት ቆዩ’ መባላቸውን ፖሊሶች ሲያወሩ ሰማሁ። በነገራችን ላይ በሰሞኑ እስርም ፍርዴን ከጨረስኩ በኋላ ለተጨማሪ 20 ቀናት የታሰርኩት ኢሬቻ እስከሚያልፍ ነው የሚል ግምት አለኝ።
ከዚህ በኋላ በአማራ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጅምላ ጭፍጨፋዎች በመተከል፣ በወለጋ፣ በኢሉባቡር ወዘተ ተፈፅመዋል። ከጭፍጨፋም ተሸጋግሮ ከተሞች ወድመዋል። ይህ ሕዝብ ይባስ ብሎ የአብይ መፈንቅለ መንግሥት የፈጠረውን ጦርነት ተሸካሚ ሆኗል። ሲያጠቃ አፈግፍግ እያለ ማዕከላዊ መንግሥት ተብየው እጁን ጠፍንጎ ይዞ እያስገረፈው ይገኛል።
#እስራት (ዘንድሮ)
ከነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ለ50 ቀናት ያህል በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እና በቃሊቲ ወህኒ ቤት ታስሬያለሁ። ይሄኛውን እስራት የፈረደብኝም ሆነ የከሰሰኝ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው። ይህ ችሎት የእነ እስክንድር ነጋን (5 ሰዎች) ዶሴ እየዳኘ ያለ ሲሆን ሦስት ዳኞች አሉት። የቀኝ ዳኛዋ #እጥፍ ወርቅ በረዳ ፋጀራ ሲባሉ የግራ ዳኛው ደግሞ #ፈየራ ተሬሳ ጉተማ ናቸው። #ሳሙኤል ታደሰ የመሀል ዳኛው ናቸው። ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ወይም/እና ቤተ መንግሥቱ ከጀርባ እንዳለ ቢጠረጠርም ከሳሾቼም ፈራጆቼም እነኝህ ግለሰቦች ናቸው።
የክሱ መሰረታዊ ሃሳብ በእነ እስክንድር ዶሴ ላይ በባልደራስ ጋዜጣ የፃፍኩት ሀተታ ነው። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ማለትም እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ የተከሰሱበት ተግባር ሀሰተኛ መሆን እና ክሱ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ የሚያትት መጣጥፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዳኞች ከገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች ቀጥተኛ ትዕዛዞችን እየተቀበሉ የሚፈርዱ መሆናቸውን ያተተ ሲሆን እስረኞች በወህኒ ቤት እየደረሰባቸው ያለውን የመብት ረገጣም አንስቷል። የዳኞች ክስ “ታማኝነታችንን አጥፍተሃል። ከአስፈፃሚው የመንግሥት አካል ትዕዛዝ አልተቀበልንም” የሚል ነው።
በዚህ ጉዳይ አንደኛ ተከሳሽ ሆኘ በደረሰኝ የመጥሪያ ደብዳቤ መሰረት ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከላይ በተጠቀሰው ችሎት ቀረብኩ። በዚሁ ዕለት ከእነ እስክንድር ጠበቆች መካከል አንዱ ቤተማርያም አለማየሁ ሁለተኛ ተከሳሽ ሆኖ ሲቀርብ አሐዱ ራዲዮ ሦስተኛ ተከሳሽ ሆኖ በሥራ አስኪያጁና በጠበቃው ተወክሎ ቀረበ። ቤተ ማርያምን ቃለ መጠይቅ አድርጎ አሐዱ በሠራው ዜና ላይ “ችሎቱን ፖለቲካዊ ነው ብላችኋል” የሚል ነው የ2ኛ እና የ3ኛ ተከሳሾች ክስ። አሐዱ ጉዳዩ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ መብት ጋር እንደሚያያዝ ካስረዳ በኋላ “ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚዳኝ ችሎት” ለማለት አስቦ “ፖለቲካዊ ችሎት” ማለቱንና ይህም ዘጋቢው ባለማወቅ የፈጠረው ስህተት እንጂ ችሎቱ ፖለቲካዊ ነው ብሎ እንደማያምን በገደምዳሜው በማስረዳቱ በነፃ ተሰናበተ። በተጨማሪም ቢሮ ተጠርቷል፤ ዳጎስ ያለ ምክር ሳይቀበል አይቀርም። ጠበቃ ቤተማርያምም ቃለ መጠይቅ የሰጠበት ራዲዮ ጣቢያ በነፃ ተሰናብቶ እርሱ ሊከሰስ የሚችልበት ምክንያት ባለመኖሩ በነፃ ተሰናብቷል። ሆኖም ክሱ ግን ፖለቲካዊ ነው ብሎ እንደሚያምን፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በችሎት ላይና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ሲናገር መቆየቱን አብራርቷል። ወደፊትም ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከማስረገጥም በላይ እነ እስክንድር ነጋ ለያዙት ሀቅ ሲል ከጥብቅና ሥራው በተጨማሪ የመብት አቀንቃኝነት ተግባሩንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል። እስከዚያ ዕለት ድረስ የነበረው የመብት ተቆርቋሪነት እንቅስቃሴ አነስተኛ በመሆኑ እንደሚቆጭም ገልጿል። አሁን ወደ ራሴ ዶሴ ልመለስ፦
በመሀል ዳኛው ችሎት ላይ የተነበበው ዘለግ ያለ መጣጥፍ “መንግሥት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የመሰረተው ሀሰተኛ ክስ በአስቸኳይ ይቋረጥ” የሚል የርዕሰ አንቀፅ ርዕስ አለው። የተነሱት የክስ ጥያቄዎች ሦስት ናቸው፦
1ኛ. የፍርድ ቤቱን ተዓማኒነት መንጠቅ
2ኛ. የዳኝነት ነፃነት እንደሌለ መጥቀስ
3ኛ. ኢ-ሚዛናዊ ትንታኔ መኖር ናቸው።
#መልሶቼ
የፍርድ ቤቱን ተዓማኒነት በተመለከተ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በተደጋጋሚ ስዳስሰውና ስገመግመው እንደኖርኩ አስረዳሁ። ፅሁፉም የግምገማው ውጤት ሲሆን ዳሰሳዎቼ ሁሉ ያረጋገጡልኝ ችሎቱ ገለልተኛ አለመሆኑን እንደሆነ ጠቅሻለሁ። “በፅሁፉ እንደገለፅኩት መንግሥት እነ እስክንድር ነጋን እና ባልደራስን ለመውጋት ዐቃቤ ሕግን እንደ ጦር፣ ፍርድ ቤቶችን ደግሞ እንደ ጋሻ እየተጠቀመ መሆኑን አምንበታለሁ። ወደፊትም በድጋሜ ልፅፈው እችላለሁ” አልኩ። በዕለቱ በዋለው ችሎት ሰብሳቢ ዳኛው የተለመደ ርጋታቸውና አባቱ እንደተቆጣው ልጅ መቅለስለሳቸው ከትሕትና ጋር
GtyeBald, [11.10.21 22:51]
እንደተጠበቀ ቢሆንም ሌሎች ሁለቱ ዳኞች ግን ከወትሮው በተለየ ፍጥነት እና ትኩረት ይታይባቸው ነበር። ጥያቄዎቹ ሲጠቃለሉ ሦስት ፈርጅ ይኑራቸው እንጂ ከላይ ከላይ ሲጠይቁኝ የነበሩት እነኝህ ናቸው። በጥቅሉ በዕለቱ ችሎት የተሰየሙት ሦስቱም ዳኞች ናቸው ከሚባል ይልቅ እጥፍወርቅና ፈየራ ከሳሽ ዐቃቢያነ ሕጎች፤ ሳሙኤል ደግሞ ወላዋይ ዳኛ ነበሩ ቢባል ገላጭ ነው።
#ሚዛናዊነት ሲባል
በጋዜጠኝነት ሚዛናዊነት (balance) ሲባል የዜጎች ፍትሐዊ የሚዲያ ተገልጋይነት ማለት ነው። አንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ለጥቂት ወገኖች ብቻ ድምፅ እንዳይሆንና ሌላው ወገን እንዳይታፈን የሚያትት ነው። ሚዛናዊነት ከዜና አላባውያን፤ ምናልባትም ከጋዜጠኝነት አላባውያን መካከል አንዱ ነው። ሆኖም ሚዛናዊ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ሙያው ይመክራል እንጂ ጋዜጠኛም ይሁን ሌላ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ “ለምን ሚዛናዊ አልሆንክም” ተብሎ በሕግ አይገደድም። እርሱ የሰሜን ዋልታ ልሳን ነኝ ካለ፤ ደቡብ ዋልታ እንዲሄድ ወይም የምድር ወገብ ላይ እንዲቆም ሕግ አያስገድደውም።
ሙያና ሙያተኝነት የሚከበርበት ሀገር ሲሆን የሙያ ማሕበራት ይህንን ሊገሩና የአስታራቂነት ሚናውን ሊወስዱ ይችላሉ። ዜና ከቤተመንግስት ተፅፎ በሚመጣባት ኢትዮጵያ ግን የሚዛናዊነትን ጉዳይ አንስቶ የሚከስ ዳኛ ሸረኛ እንጂ የሕግ ባለሙያ ሊሆን አይችልም። ስለ ጋዜጠኝነት የሙያ ስነ ምግባር ከመጨነቁ በፊትም የሕግ ሙያዊ ስብዕናውን ሊሸጥ አይገባም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሚዛናዊ መሆን ተገቢ ነው በሚል ተስማምተን እንቀጥል። ከላይ በስም የተጠቀሱት ሦስት ዳኞች የመንግሥት ሹመኞች ናቸው። መንግሥት ደግሞ ራሱ የሚዲያ ባለቤት ነው። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተባሉ አንደበቶች አሉት። እነኝህ በውስጣቸው በርካታ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ያሏቸው ናቸው። የየብሔሮች መገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች አሉ። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ዋልታ ቴሌቪዥን የተባሉ የገዥው ፓርቲ ንብረቶች አሉ። 3ቱ ሹመኛ ዳኞች ከጠቀስኳቸው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አንደበቶችን መጠቀም ይችላሉ። ድምፅ አልባ አይደሉም። ጋዜጠኝነት ደግሞ የድምፅ አልባዎች ድምፅ እንጂ የመንግሥት አጃቢ አይደለም። በመሆኑም የነፃገት ታጋዮች፤ የግፍ እስረኞች ድምፅ ነኝ ስል ሹመኞች ለእኛም ጩህ ሊሉኝ አይገባም።
በአጠቃላይ ክሱ እነ እስክንድር ነጋን ታሪክ አልባ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው። ይህ የግፍ ክስ፣ የግፍ እስር፣ የግፍ ችሎት ታሪኩ ዕለት በዕለት ተሰንዶ ለመጭው ትውልድ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ያለመ ነው። ለጊዜው አልተሳካም።