በኦሮሚያ ክልል በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ፕሮግራማዊ ተልእኮ እየተመራ ያለው የአማራን ዘር የማጥፋት ኢ-ሰብዓዊና አፀያፊ ድርጊት ሊቆም ይገባል
ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ከጭጨፋ የተረፉ የ19 ቀበሌ ነዋሪዎች 40 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ መጠለላቸው ታውቋል፡፡ ከሞት አምልጠው ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁንም ለሕይዎታችን አስተማማኝ ነገር የለም በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ዓመታትን ያስቆጠረው የአማራ ተወላጆች ጭፍጨፋ አሁንም ድረስ መፍትሔ ያላገኘው፣ ጥቃቱ በኦህዴድ/ብልፅግና መንግስት የሚመራ በመሆኑ እንደሆነ ገሃድ እየወጣ መጥቷል፡፡
በሆሮጉድሩ ወለጋ በጃርቴ ጃርዴጋ ወረዳ በሻምቡ ከተማ እና ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ በዚህ ሳምንት ከፍተኛ ጥቃት ከተደረገባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ ምስራቅ ወለጋ ዞን የጊዳ ኪረሙ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው ኪረሙ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳያውሉ እንቅፋት ፈጥራችኋል በሚል ሰበብ ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በጅምላ መረሸናቸውን ከጅምላ ጭፍጨፋው አምልጠው የወጡ የአይን እማኞች መናገራችው በሚዲያ ተዘግቧል ።
ከህዳር 09/2015 ዓ/ም ጀምሮ በከተማዋ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ እስረኞች ህዳር 20 ለህዳር 21 አጥቢያ በጅምላ መረሸናቸው አይዘነጋም። በህዳር ወር ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ሽብርተኛው ሸኔ እና የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ተቀናጅተው ባካሄዱት ኢ- ሰብአዊ ዘመቻ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሕይወታቸው ተቀጥፏል፤ከፍተኛ መፈናቀልም ደርሶባቸዋል፡፡
አማራን የመጨፍጨፍ እና የማፈናቃሉን አፀያፊና ዘረኛ ድርጊት የሚያስተባብሉ እና ሥራዬ ብለው የሀስት ዘመቻ የሚያናፍሱ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች፣ በተለይም የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግሬስ ሁለቱ ምክትል ሊቃነመናብርት እና የኦነግ የተለያዩ ክንፎች መሪዎች እና እነሱ የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጀው ከሕወሓት ቡድን ጋር በደቡብ አፍሪካ መደራደሩን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የአማራዎች ጭፍጨፋ ተጠናክሮ መቀጠሉ የአደባባይ ክንውን ሆኗል፡፡ የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚዪኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በቅርቡ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ መንግስት ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ሽብርተኞች ጋር እንደማይደራደር እና ከአባ ገዳዎች ምሕረት ጠይቀው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን መግለፁ አይዘነጋም፡፡ ይህ አባባል የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በስውር ባሰማራው በሸኔ ላይ የሚጨክን ልብ የሌለው መሆኑን በግልፅ ያመለክታል፡፡ በተለይም በምስራቅ ወለጋ እና በአካባቢው ግድያ እና ዘረፋው አሁንም እየቀጠለ መሆኑን የሚገልፁት የጥቃቱ ሰለባዎች፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሕይታቸውን ለማትረፍ ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ ተጠልለው የሚገኙ ንፁሐንን መንግሥት የመከላከያ ሰራዊትን ወደ ቦታው ድረስ ልኮ ከሞት እንዲታደጋቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አዳማጭ መንግሥት ያላገኙ ስለመሆኑ በገሃድ እየታዬ ነው፡፡
የተለያዩ ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች መንግሥት ለምን ከሼኔ ጋር አይደራደርም በሚል ድርድር እንዲካሄድ እየገፋፋ ይገኛሉ፡፡ አማራ ኦሮሞን በቅኝ ግዛት ገዝቶታል በሚል የሃሰት ትርክት አስተሳሰባቸውን ያዛቡባቸውን የኦሮሞ ወጣቶች “ፋኖ ወደ ኦሮሞ ክልል ገብቶ ግድያ እየፈፀመ ነው” በሚል የሃሰት ዘመቻ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ተማሪዎች አመፅ እንዲቀሰቀሱ በመገፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ዘመቻቸው የአመለካከት አምሳያቸው የሆነው ህውሓት በፋኖ ላይ የከፈተውን የሃሰት ውንጀላ በማጠናከር የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን በፋኖ ላይ እንዲያዘምት በመቀስቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
እንደሚታወቀው በወለጋ እና በሰሜን ሸዋ አካባቢ እራሳቸውን ከህልውና ጥፋት እየተከላከሉ ያሉት በግፍ መገደልና መጠቃት ያንገሸገሻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንጅ ከአማራ ክልል የተነሱ ፋኖዎች እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ የፋኖን ስም ማጠልሸት የኦነግ – ብልጽግና፣ የኦነግ፣ የህወሓት እና የኦፌኮ የቀን ተቀን ተግባር መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ይህም እነዚህ ድርጅቶች ከአማራ የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እና በኢትዮጵያ ክስመት የትግራይ እና የኦሮምያ ሪፖብሊኮችን ለማዋለድ ሲመሠረቱ ጀምሮ ይዘው የተነሱትን የፖለቲካ ዓላማ እስካሁን ድረስ እያራመዱት እንደሚገኙ የሚያሳይ ተጨባጭ ክንውን ነው፡፡ ይህ አካሄዳቸው ህወሓት፣ ኦህዴድና ኦነግ የፖለቲካ ዓላማ አንድነት ያላቸው ፀረ- ኢትዮጵያ ድርጅቶች መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡
ፓርቲያችን ባልደራስ በወለጋም ሆነ በሌሎች የኦሮምያ አካባቢዎች ማቆምያ በሌለው ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የአማራን ዘር የማጥፋት መንግሥታዊ መር ዘመቻ በፅኑ እየተቃወመ፣ የአማራው ማህበረሰብ ህልውናውን ከጥፋት ለመከላከል እያደረገ ያለው ተድጋሎ ተገቢ እና ህጋዊ መሆኑን በመግለፅ፣ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ባልደራስ የዩኒቨርስቲ መምህራን የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ ለመብታቸው መከበር እያደረጉ ያሉት ተቃውሞ ህጋዊ እና ሰላማዊ በመሆኑ፣ ከጎናቸው የሚቆም መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል፡፡