ማን ያልቅስለት? (ስንታየሁ ቸኮል፤ የኅሊና እስረኛ ከቂሊንጦ)
ወገኖቼ ለሚሞተው የዐማራ ህዝብ
ማን ይጩኽለት? ማን ያልቅስለት?
ማን በክብር ይቅበረው? መጠየቅ ያስፈልጋል።
ህገ-መንግስቱን እናስጠብቃለን ባዮችና ምለው የተገዘቱ መሪዎቹ
በአዲስ ምዕራፍ ፤ የወይን ጠጅ ስካር፥ ሁሉም ህዝቡንም ራሱንም ላይመለስ ክዷል፥ አንዱ በዘውድ ክብር ሌላው በንዋይ እቡይነት ድሆቹ ተረስተዋል።
ድርጅቶቹና መሪዎቹ የት ገቡ?
ስለእኛ ፍትህ እጦት ‘ይፈቱ’ ጥያቄ በማህበራዊ ሚዲያ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በሰማንበት ቅፅበት ከደም መሬቱ ወለጋ በዐማራ ህዝብ ላይ በተደጋጋሚ በኦህዴድ/ብልፅግና የሰለጠነ ኦነግ ሸኔ በተባለ ፥ አራጅ ቡድን ግፉዓን የዐማራ ተወላጆች በማንነታቸው ብቻና ብቻ እየወደቁ እንዳለ መስማት ለጆሮ እንኳን ይከብዳል። ግን ለምን?
“ክፉ ሰርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ
መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል” ይላል ቅዱስ ጴጥሮስ በትምህርቱ።
ጀግና ግፍ መስራት ሳይሆን ግፈኞችን መታገል ነው ሚናው። በዚች ሁለት ቀን ከወደ ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ አዲስ ዓለም ቀበሌ በዐማራ ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተጠያቂው ማነው? በማለት እንጠይቃለን። ዐቢይ አህመድ በአዲስ ምዕራፍ ጭፍጨፋውን አጠናክሮ ለመቀጠሉ የሚጠራጠር እንዴት ይኖራል? ይሄን እንድንለማመደው የሰጠን የሁልጊዜ ሞትና መፈናቀል ከሞታችን በላይ፤ ንጉሠ ነገሥቱ እንዳይቀየሙ በሚሉ መስፍኖች ዝምታችን ፈራሁት፥ እነዚህን ሳስብ መንፈሴ በሀዘን ስብራት ከዳኝ። እነዛ በዛ ሀሩር ጫካ የወደቁ ህፃናት፣ እነዛ የጣር ድምፆች የድረሱልን ጥሪ ያሰሙ አረጋዉያን ፣ እነዛ በየጫካው መቀነታቸውን አስረው የሚጮሁ እናቶችን ሳስባቸዉ መሪ እንደሌለው መንጋ እንደገደል ማሚቶ ድምፃቸዉ ለራሳቸው ሲያስተጋባ ማሰቡ እጅግ ያሳዝናል። ኧረ ኡፍፍፍ!
ኦህዴድ/ብልፅግና የተባለ መርዝኛ ድርጅት በመንፈስ አባቱ ኦነግ ሸኔ_ ዐማራን የማጥፋት ተልዕኮ ከእናት ድርጅቱ ውርስ በወሰደው ክፉ ሴራ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ይህን በአይናችን እየተመለከትን የዐማራ ሊሂቃን ዝምታው ያስተዛዝባል። አውቆ በማልመጥ እና በጥቅም በመታወር የሹመት ድንዛዜ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፍዘት ውስጥ ገብቷል። በወለጋ ጫካ እንደ ጎርፍ የሚፈሰው እነዚህ ዐማሮች ሞታቸው አንገብግቦት ሬሳቸው በጅብ ሲበላ የቆመ ድርጅት የለም። ይመለከተኛል የሚል የክልሉ መንግስት ስለሟቾቹ ዜና መስማት አይፈልግም። በኦህዴድ/ ሸኔ መንግስታዊ ድጋፍ በሰራዊትና በሎጀስቲክ የታገዘ ግድያ ሲፈፀም ያለንበት የመከራ ዘመን እንዴት አይነት የፈተና ጊዜ እንደሆነ ማየት ይቻላል።
እኔ እንደ አንድ ወገን ሁሉም ሰዉ መንግስት አልባ ስለሆኑ እነዚህ ንፁሓን ዐማሮች መጮህ ይገባዋል። የሚሞተው የሰዉ ልጅ ነው እየወደቀዉ ያለው አንገቱ ላይ ባለ ማሕተብ ነው። የሚሞተው አምላኩን በመፍራቱ ነው። የሚሞተው ፍርሃ እግዜር ስላለው በደልን ስለሚጠየፍ ነው።
ይህን እስከመቼ እንታገስ?
በድሆች ሞትና መፈናቀል አዝኜ ራሴን ለማፅናናት ይችን በቅዱስ መፅሐፍ አገኘሁ፦ “ወዳጆች ሆይ እናንተ የተወደዳችሁ ብርቱዎች መከራ በመቀበላችሁ የክርስቶስ መከራ ተካፋይ በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ” ተብሎ እንደተፃፈው በመከራችሁ መሪር ሐዘን ተሰምቶኝ ጩኸታችሁን አምላክ ይመለከት፤ ፍርድም ይሰጥ ዘንድ በፈጣሪ ዘንድ ከልብ እማፀናለሁ። በቃ ይለን ዘንድ ትጉና ለምኑ እንደተባለው ማለቴ ነው።