ለእውነተኛ ፍትህ የሚጨነቅን ሰው በፍትህ ዕጦት ማስጨነቅ የግፍ መጨረሻ ነው !!
የባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ባልተገኙበት ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱ ተገቢነት የለውም።
አቃቤ ሕግ ምስክሮችን በግልፅ ችሎት አቅርቤ ምስክር ማሰማት አልችል በማለት ሰበብ መሪዎቻችን የተፋጠነ ፍትህ እንዳያገኙ እየሰራ መሆኑን ከጅምሩ ፓርቲያችን ይረዳል።
ጠ/ፍ/ቤቱ የቀጠሮ ቀን ከመወሰኑ አስቀድሞ የመከራከሪያ ጭብጡን ግልባጭ ጠበቆቻችን በተደጋጋሚ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል።
ግልባጩ ለተከሳሽ የባልደራስ አመራሮችም ባልደረሰበት ሁናቴ ዛሬ ጠ/ፍ/ቤቱ ለቀጣይ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ግራ ቀኙን ለማከራከር በሚል ቀጠሮ ሰጥቷል።
ይህ ደግሞ አመራሮቻችን የተፋጠነ ፍትህ አግኝተው በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ተሳትፈው በህዝብ እንዳይዳኙ ሆን ተብሎ ዕንቅፋት መፍጠር መሆኑን ተገንዝበናል። ህዝቡም ይረዳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፤ ገና ከጅምሩ የፍትሕ ሥርዓቱ በሕግ እና በእውነት እንዲመራ የዛሬን ብቻ ሣይሆን የወደፊቱን ጭምር በማሰብ ፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ፥ ” ይህ እንደ-ማናቸውም የወንጀል ጉዳይ አይደለም ፤ ይህ ታሪክ ነው ። ነገ በታሪክ የሚጠቀስ የፍትሕ ሥርዓት ነው ።
ከሁሉም በፊት ፤ ሁሉንም በሚያውቀው በፈጣሪ ፊት ! እንዲሁም በህዝብ ፊት ጥፋተኞች አይደለንም ። ፈጥኖ ይሁን ዘግይቶ ነፃ እናወጣለን!
ጊዜው የምርጫ ነው ፤ የሚጠብቀን ህዝብ አለ ፤ በህዝብ መዳኘት እንፈልጋለን ። ለምርጫ እየተዘጋጀን ባለንበት ወቅት ነው በሐሰት ክስ የታሰርነው ፤ ይህን ፍርድ ቤት ፤ በፈጣሪ ስም እና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የምንጠይቀው የተፋጠን ፍርድ እንዲሰጠን ነው ። ” በማለት እስክንድር ገና ከጅምሩ አጽኖት በመስጠት በፍ/ቤት የተናገረው ቃል ነው !!!
በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ የአገራችን የፍትህ ስርዓት የቀብር ዋዜማ ላይ መሆኑን በመረዳት ፤ በቀጣይ ለምናደርገው ማንኛውም ሰላምዊ ትግል ከጎናችን እንዲሆን እንጠይቃለን!
ባልደራስ ከያዛቸው ሰላማዊ ትግሎች አንዱ በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ ነው። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፤ በምርጫ ካርዱ ሰለዕውነተኛ ፍትህ እንዲተጋ እንጠይቃለን!
ድል ለዴሞክራሲ
ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
የካቲት 2013